በአማራ ክልል በሁሉም አከባቢዎች መልካም አስተዳደርን በተመለከተ የህዝብ ግምገማ እየተደረገ ሲሆን በዚሁ
ግምገማ የመንግስት ባለስልጣናት ክፉኛ በሙስና ተጨማልቀዋል የሚል ክስ በተሰብሳቢው ህዝቡ እየቀረበ ነው።
በዳንግላ ከተማ በተካሄደው ተመሳሳይ ስብሰባ ህዝብ በረሃብ እየተሰቃየ ባለበት በአሁኑ ወቅት የህዝብንና
የሃገርን ንብረት ዘርፈዋል በሚል ክስ ከቀረበላቸው የመንግስት ባለስልጣናት መካከል አቶ ኩማ ሚደቅሳ በአ/አበበ ከተማ በካሳንችስ
አከባቢ ቪላ ቤት እያስሰሩ መሆናቸውን ፤ አቶ ምህረት ደበበ ለመብራት ሃይል ተብሎ ከሚመደበውን በጀት ከፊሉን ለግል ጥቅማቸው በማዋል
በአመሪካ ባለ አራት ኮኮብ ሆቴል መክፈታቸውን እንዲሁም አቶ በረከት ስምኦን ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ 60 ሚልዮን ዶላር በለንደን
በሚገኝ አንድ ባንክ ቤት አስቀምጠዋል የሚል ይገኝበታል።
በስብሰባው ተገኝተው በባለስልጣናቱ የተፈጸመውን ሙስና ያጋለጡት አቶ ጋሻው አንዳርጌና አቶ እያሱ መንግስቱ
የተባሉ ተቀማጭነታቸው በውጭ ሃገር የሆኑና ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ወደ ሃገር ቤት በቅርብ የመጡ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ግለሰቦቹ
ስብሰባው ከተጠናቀቀ ብሁዋላ ትፈለጋላችሁ ተብለው በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተወስደው ደብዛቸው መጥፋቱንና በተለያዩ አከባቢዎች
አፈላልገው አድራሻቸውን ማግኘት ያልቻሉት ቤተሰቦቻቸውም በጭንቀት መዋጣቸውን ከቦታው የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።