Tuesday, February 25, 2014

የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ትህዴን) የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ



በአገር ውስጥና ካገር ውጭ ለሚገኘው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ለጀግናው የትህዴን ሰራዊት፤ ለትግሉ ደጋፊዎችና ኣባሎቻችን እንኳን ለ13ኛው ዓመት የትህዴን ምስረታ ኣደረሳቹህ ኣደረሰን።
እንደሚታወቀው አገራችን ብልሹ በሆነው የህወሓት ኢህአዴግ የአስተዳደር ስርአት ስር ከገባች እንሆ 23 ዓመታት ብታስቆጥርም በስልጣን ላይ ባለው አምባገነን መንግስት ምክንያት የሃገርና የህዝብ እድገት ሊረጋገጥ አልተቻለም።ምክንያቱም የአንድ አገር እድገትና ግስጋሴ የሚለካው ስርዓቱን በሚሎው ያለ የማዳናገርያ እድገት ሳይሆን የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ተሻሽሎ ዜጎች እኩል የሃብት ተጠቃሚ ሆነው በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ብቻ ነው።፣ በአገራችን ላይ ያለው ስርዓትና እየተከተለው ያለ መንገድ ግን ከዚህ ሃሳብ ጋር የማይሄድ ነው ብቻ ሳይሆን በምን ብልሃት  የህዝቡን መብት አፍነንና ጨፍልቀን የሃገር ሃብት ወደ ግል ይዞታችን እያስገባን እንቀጥል የሚል አስተሳሰብ ተንሰራፍቶ ይገኛል።
 በአሁኑ ግዜ ስርዓቱ ምንም ዓይነት ህዝባዊ አመለካከት በሌለው መንገድ ለመጓዝ ስለሚፈልግ ሁሌ ከተንኮልና ከክፋት የሚመነጭ አሰራር ሲያራምድ ይታያል ነገር ግን እነዚህ አምባገነኖች ካለፉት ስርዓቶች የማይማሩ ሆነው እንጂ ህዝቡን በሃይል አፍነህ በማንበርከክ የስልጣን እድሜ ማራዘም እንደማይቻል ከትናንቱ ታሪክም መማር በተገባቸው ነበር። “አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲሉ የህወሓት ኢህአዴግ አመራሮች አውቀው እየፈፀሙት ባሉ ብልሹና አፋኝ የአገዛዝ ስርዓት ምክንያት ህዝቡ ባላዩ ላይ እየተፈፀመ ባለው የሚያንገፈግፍ በደል ተነሳስቶ በባዶ እጁም ሳይቀር እየታገለና እየተቃወመ ያለበት ሁኔታ ላይ ይገኛል።
 የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔ ስርአት በሰላማዊና ፖለቲካዊ ትግል  ከስልጣኑ ማባረር እንደማይቻልና ለህዝብና ለሃገር ቅንጣት ያህል እንኳን በማያስብ በግል ጥቅም የሰከረ ስግብግብ ፍላጎቱን ማረጋገጥ እንደማይችል አበጥሮ ያውቃል ብቻ ሳይሆን በሰላማዊና ፖለቲካዊ መንገድ ለውጥ እናመጣለን ብለው ለሚንቀሳቀሱ ወገኖችም ሳይቀር ባገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ ይዘውት ባሉት መንገድ ለውጥ ማምጣት እንደማይችሉ በግልፅ ተናግሯል ይህ ደግሞ ድርጅታችን ትህዴን ከ13 አመት በፊት ለወሰደው ከፀና እምነት የመነጨ የትጥቅ ትግል አቋም የሚያጎለብት ሲሆን በሌላ በኩል የወያኔ ኢህአዴግ እድሜ የሚያሳጥር መንገድ እንደሆነም የሚያጠራጥር ኣይደለም።
 ክቡር የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ!
ባለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት ውስጥ ካለፉት የአገራችን ስርዓቶች በከፋ መልኩ የህወሓት ኢህአዴግ ስርዓት ከፍተኛ የመብት ረገጣና መጠነ ሰፊ በደሎች በላይህ ላይ እየፈፀመ መጥቷል የኢህአዴግ መሪዎች አጋጥሞህ ካለው የማህበራዊ ችግርና አጠቃላይ አገሪትዋ ከገባችበት የድህነት ማቅ ለማስወጣት ጥረት ከማድረግ ይልቅ መጨረሻ የሌለው የገንዘብ መዋጮና ፍትሃዊነት የጎደለው ግብር እንድትከፍል፤ የመልካም አስተዳደር እጦትና የስራ አጥነት ችግር እንዲስፋፋና ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች በመከሰታቸው ምክንያት ተሰቃይተህ አገርህን ትተህ እንድትሰደድ እያደረጉህ ይገኛሉ።
በአሁኑ ግዜ በሚገርም ሁኔታ የህወሓት ኢህአዴግ ባለስልጣናት ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ  ባለው የህዝብ ድጋፍና አስደንጋጭ በሆነው የህዝብ ተቃውሞ ስጋት ላይ በመውደቃቸው የተነሳ ቀጣይ አመት ለሚያካሂዱት የይስሙላ አገራዊ ምርጫ ለማደናገር ያመቻቸው ዘንድ የበግ ቆዳ ለብሰው ተሳስተን ነበርን ይቅር በለን እያሉህ ይገኛሉ። ይህ አባባል የተለመደና ለአገራችን ህዝብ አዲስ ነገር ባይሆንም አሁንም ቀጣዩ የምርጫ ወቅት እስክያልፍ ድረስ እየተጠቀሙበት ያለ ህዝቡን ያሰለቸ ብልሃት መሆኑን ሳትደናገር በአገራችን ውስጥ ሰላምና ዴሞክራሲ ሊሰፍንና መሰረታዊ ለውጥ እንዲረጋገጥ ከተፈለገ በወያኔ ኢህአዴግ መቃብር ብቻ መሆኑን አውቀህ አደረጃጀትህ በማጠናከር ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ት.ህ.ዴ.ን/ ጎን ሆነህ ስታካሂደው የቆየህውን ሁለንተናዊ ድጋፎች አጠናክረህ እንድትቀጥልበት ት.ህ.ዴ.ን በዚህ ኣጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል። 
     የተከበርክ ጀግናው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሰራዊት!!
 ባለፉት የትግል ጉዞ ውስጥ እየከፈልከው የመጣሀውን መስዋእትነትና በሚገርም ጀግንነት እያስመዘገብከው የመጣህ ታላላቅ ድሎች ድርጅታችንን ወደ ትልቅ የእድገት ጎዳናና ግስጋሴ አድርሷል ይህ ደግሞ የሰነቅከው ህዝባዊ አመለካከትና የተነሳህለትን የአላማ ፅናት የሚያመለክት ነውና አሁንም የጀመርከው ህዝባዊ ትግል መጨረሻው ላይ እስኪደርስ ድረስ ሳትሰላች ህዝባዊ ተጋድሎህን ማጠናከር ይገባሃል በዚህ አጋጣሚም እንኳን ለ13ኛው ዓመት የካቲት 19 የድርጅታችን ምስረታ አበቃህ ለማለት እንወዳለን!
 የተከበራቹሁ የተቃዋሚ ድርጅቶች!
 የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ ባለፉት 13 የትግል ዓመታት ውስጥ በአምባገነኑ የኢህአዴግ ስርዓት ላይ ትላልቅና አንፀባራቂ ድሎች እያስመዘገበ መጥተዋል ትህዴን ከመጀመርያውም ጀምሮ የኢህአዴግ ስርዓት በትጥቃዊ ትግል እንጂ በሰላማዊና ፖለቲካዊ ትግል እንደማይገረሰስና የህዝቡንና የአገራችን ችግር እንደማይቀረፍ የማያወላውል አቋም ይዞ በተደጋጋሚ እየገለፀ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ለዚህ ተጨባጭ መፍትሄ ማምጣት የሚችል መንገድ ባለ-መከተላችንና ተባብረን ውጤት ያለው ስራ ባለ-መስራታችን ምክንያት የሚፈለገው ያህል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም ስለዚህ በሁለቱም ጫፎች ያለነውና ስርዓቱን እየታገልነው ያለነው ድርጅቶች ለህዝቡ ለውጥ እንድናመጣለትና ካለው አፋኝ ስርዓት ልናድነው ከሆነ  አሁንም ትብብራችን ማጠናከርና ለውጥ ማምጣት የምንችልበት መንገድ መከተል ግድ ይለናል።
በዚህ አጋጣሚም ትህዴን አሁንም እንዳለፈው በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ከሚያምኑና የኢህአዴግን ስርዓት በመቃወም ከሚታገሉት ድርጅቶች ጋር ለውጥ ማምጣት በሚያስችል ስራ ላይ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
ደግመን እንኳን ለየካትት 19/13ኛው የትግል ዓመትና የትህዴን ምስረታ በዓል አደረሰን ኣደረሳቹህ።    
                          
                              ለማይቀረው ድል በፅናት እንራመድ!
                                  ድል ለጭቁኖች!
                   የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ት.ህ.ዴ.ን/
                                       የካቲት 19 / 2006 ዓ/ም