Wednesday, February 25, 2015

የካቲት 19/2007 14ኛ ዓመት የትጥቅ ትግል ምስረታን ምክንያት በማድረግ ከትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ!!



በውስጥና በውጭ ለሚገኘው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ለጀግናው ሰራዊታችን፤ ለድርጅታችን አባላትና ለትግላችን ደጋፊዎች እንኳን ለ14ኛው ዓመት የትጥቅ ትግል የምስረታ በዓላችን አደረሰን አደረሳችሁ።
    የትጥቅ ትግል ሲባል ከባድና ትልቅ ዋጋ የሚጠይቅ እንደሆነ የሚስተው ስብዓዊ ፍጡር የለም። ምክንያቱም ተገድደህ የምትገባበት የመጨረሻ አማራጭ ስለሆነ ድርጅታችን ከ14 ዓመት በፊት እንደዛሬው ይህንን የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የትጥቅ ትግል የጀመረው ህዝባችን የታገለለትንና ከባድ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ያገኘውን ድል ተቀምቶ ለግለሰቦች የግል ጥቅም ማረጋገጫ በመዋሉ ነው።
    የህወሃት መሪዎች የህዝባችንን ትግልና መስዋዕትነት ተጠቅመው ስልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ የህዝቡን ፍላጎትና ጥማት ወደ ጎን በመተው ህዝቡን እንዴት የትግል ውጤቱ ተጠቃሚ እናድርግ ከማለት ፋንታ እንዴት አድርገን የስልጣን እድሜያችንን እናስረዝም፤ የግል ጥቅማችንን እንዴት እናሳድግ የሚል ፈሊጥ በመከተል ለበርካታ አመታት የተካሄደውን ትግል ፍሬ አልባ ሆኖ እንዲቀር አድርገውታል።
    ድርጅታችን የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ይህንን በህወሃት መሪዎች የተፈፀመ አሳዛኝና አስደንጋጭ ክህደት አንገትን በመድፋትና በማዘን የሚፈታ ባለመሆኑ የሰማዕታትን አደራና የመላው ህዝባችንን ጥሪ ለመመለስ ዳግም የካቲት 19/ 1993 ዓ/ም የትጥቅ ትግል እንዲጀምር ተገዷል።
    የህወሃት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርዓት በ24 ዓመታት የእድሜ ስልጣኑ በህዝባችንና በሃገራችን ላይ ትላልቅ ወንጀሎችን  ሲፈፅም እንደቆየ የሚታወቅ ሲሆን አሁንም ሳይጀመር የተጨረሰ በግንቦት ወር 2007 ዓ/ም አካሂደዋለሁ እያለ ነጋ ጠባ የህዝብን ጆሮ በሚያደነቁረው የምርጫ ሂደት ላይ  በአንድ በኩል የበግ ለምድ ለብሶ ሰላማዊ ምርጫ አካሂዳለሁ በማለት ካለፈው ዓመት ጀምሮ እስካሁን ህዝብ በመጨፍጨፍና በህብረተሰቡ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸውን ወገኖች በማሰርና በማፈን ተግባር ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።

    ስለሆነም  ድርጅታችን ይህንን ያለ ህዝብ ፍላጎት በስልጣን ላይ የሚገኘውን አምባገነን ስርዓት በሰላማዊ መንገድ ከስልጣኑ ሊወገድና የመላውን የሃገራችንን ህዝብ ጥያቄም ሊመልስ አይችልም ብሎ ስላመነ የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የትጥቅ ትግል እንዲከተል የተገደደውና አሁንም እየቀጠለበት የሚገኘው።
    የተከበርህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ለአመታት ስታካሂደው የቆየኸው ትግልና የከፈልህው መስዋዕትነት  የአምባገነኖች የጥቅም ማረጋገጫና  የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ሲሆን ለአንተ ደግሞ መጨቆኛ ሆኗል።
    ይህ በስልጣን ላይ ያለው ፀረ ህዝብ ስርዓት ትላንት ለህዝቡ ጥቅም ነው የቆምኩት ይል የነበረውን አስመሳይ አንደበቱን ከድቶ በመስዋእትህ ስልጣን ጨብጦ በአፈና መረቡ ካስገባህ እነሆ 24 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፥ ዛሬም ቢሆን እየተዘጋጀ ያለውን የተጨረሰ የምርጫ ድራማ እውን ለማድረግ አንተን በተለያዩ የማይተገበሩ የስለት ቃሎችን በመደርደርና በማስፈራራት የስልጣን እድሜውን ለማስረዘም የሚያደርገውን ተንኮል በቃህ አይሆንም እንድትለውና ጥሪውን እንድታከሽፈው። የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) በዚህ አጋጣሚ መልእክቱን ያስተላልፋል።
    የተከበርህ ጀግናው ሰራዊታችን! በአለፉት 14 ዓመታት የትግል ጉዟችን በፀረ ህዝብ የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርዓት ላይ እያስመዘገብሀው በመጣኸው አበይት ድሎች የድርጅታችን እድገት ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ እንድንደርስ ችለናል፣ አሁንም መፍትሄው አጠናክረህ በያዝህውና መስዋእትነት እየከፈልክ በመጣኸው የትጥቅ ትግል ነውና። የህዝብህን ጥያቄ ለመመለስና የተሰው ሰማእታትን አደራ ከግቡ ለማድረስ ዛሬም እንደትላንቱ ህዝብህን ከጎንህ አሰልፈህ ትግልህን አጠናከረህ መቀጠል ይገባሃል።
    የተከበራችሁ የሃገራችን የተቃዋሚ ድርጅቶች! ሃገራችን በዚህ አፋኝ ስርዓት ስር ከወደቀች ይኸው 24 ዓመታት አስቆጥራ ትገኛለች፥ በነዚህ ሁለት አስርት አመታት ውስጥም በስልጣን ላይ የሚገኘው አምባገነን ስርዓት በህዝባችንና በሃገራችን ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍና በደል ፈጽሟልም እየፈጸመም ነው።




    ይህ በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው አፈናና ጭቆና እንዲቆምና እንዲቀጥል የምንወስነው እኛው በስርዓቱ ውስጥ ያለንና በተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ ትግል ላይ የምንገኝ ዜጎች መሆናችንን የማያከራክር ሃቅ ነው። ነገር ግን አላማችን ህዝባችንን ከዚህ አፋኝ ስርዓት ነፃ ማውጣት ቢሆንም አንዳንዶቻችን የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ስርዓት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሆነና በሰላማዊ መንገድ ሊወርድ እንደሚችል አድርገን በማሰብ  የስልጣኑ እድሜ አራዛሚዎች ስንሆን በትጥቅ ትግል ላይ የምንገኝ ደግሞ አንድ አካል ሆነን በጠላታችን ላይ ክንዳችንን አስተባብረን  ማሳረፍ አልቻልንም።
    ስለዚህ አሁንም አንድ አካል ሁነን ውጤት የሚያመጣ መንገድ በመከተል ፀረ ህዝብና ፀረ ሃገር ለሆነው ስርዓት እድሜውን ማሳጠር ይገባናል እያልን፥ ዛሬም እንደወትሮው ትህዴን ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን እየገለጽን በድጋሜ እንኳን ለ14ኛ ዓመት የካቲት 19 / 2007 ዓ/ም አደረሳችሁ አደረሰን እንላለን። 
 የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን)
                                   ድል ለጭቁኖች!!
                                    የካቲት 2007 ዓ/ም