Sunday, March 1, 2015

በሃገሪቱ የሚገኙ በሰላማዊ ትግል የተደራጁ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ድርጅት ጽህፈት ቤቶች እየተዘጉ መሆናቸው ተገለፀ።



    ከስፍራው የደረሰን መረጃ እንዳመለከተው በቅርቡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በመኢአድና በአንድነት ድርጅቶች ላይ በወሰደው ከምርጫ  የማገድ ተግባር ምክንያት ከዚህ በፊት በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች፤ ዞኖችና ወረዳዎች የተቋቋሙና የተዋቀሩ የአንድነት ፅህፈት ቤቶች አመራሮችና አባሎች እንዲሁም የተለያዩ ተወካዮች “ገዥው መንግስት የራሱን እቅድና ፕሮግራም ለማስፈፀም ሲል በራሱ አምሳል ከቀረፃቸው ተላላኪዎች ጋር መስራት አንችልም፤ ከእነሱ ጋር መስራት  ኢ.ህ.አ.ዴ.ግን ምረጡ  ማለት ነው ”  በማለት ቢሮወቻቸውን እየዘጉ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ የአንድነት አባላትና አመራሮችን የገዥው መንግስት ተላላኪ ፖሊሶች እየተከተሉ በአይነ ቁራኛ እየጠበቋቸው መሆኑን አስረድተዋል።
   ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ የአንድነት ፅህፈት ቤት ሃላፊዎች ከጥር 22 /2007 ዓ/ም ጀምሮ ታግደው በፖሊሶች ክትትል እየተደረገባቸው እንዳሉ በተመሳሳይ የመኢአድ አመራሮች የነበሩ አቶ ተስፋየ ታሪኩ፤ የምስራቅ ጎጃም ዞን ተጠሪ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮነን፥ የደቡብ ጎንደር ዞን ተጠሪ አቶ ጥላሁን እንዲሁም የሰሜን ጎንደር ዞን ተጠሪ አቶ ዘመነ ምህረት በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ እንግልት እየደርሰባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።