Tuesday, March 3, 2015

በወያኔ ስርዓት አካሄድ የሚደናገር ህዝብ አይኖርም!!



    ያለንበት ዘመን የሳይንስና ቴክኖሎጂ የእድገት ወቅት፤ በመሆኑ ዓለማችን በየሰዓቱ ዓዳዲስ አስደናቂ ትእይንቶችና ፈጠራዎች የሚታዩባትና ወደ ፊት እየመጠቀች ያለችበት ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ለሁላችንም ግልፅ ነው።
    ይህ እድገት የወለደው ግልፅና የሚዳሰስ ለውጥም በዚች  ምድር ላይ የምንገኘውን ፍጡራን የሳይንስ ግኝት የሆኑ ትምህርት ለሁሉም በሚል ሃሳብ በዓለም ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባር ላይ እንዲውል ቢደረግም በአምባገነኖች ስርዓት ምክንያት ግን እውነታውን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ የህብረተሰቡ እውቅና በትምህርት ጉዳይ ላይ አስፈላጊውን ዘመቻና የማነሳሳት ስራ ከማድረግ ይልቅ የስርዓቱ የትምህርት ፖሊስው በራሱ ህልውና ማረጋገጥ ብቻ እንዲቀረፅ ኣድርጓል።
ማንኛውም ዜጋ በስርዓቱ ላይ የሚያመልክ ጠባብ አመለካከት ይዞ እንዲማር ስለ ሚደረግና ከዚህ አመለካከት ውጭ ሆኖ እንዲጓዝ ካሰበም መጪው የስራው እድሉ ጠባብ እንዲሆን በማድረግ የስርአቱ አባል ወይም ደጋፊ ለመሆን የሚያስገድድ አካሄድ እንዲኖር እየተደረገ ነው።
    በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች አንዱ ብሄር ከሌላው ብሄር በጎሪጥ እየተያዩና እየተጋጩ ጠባብና ከፋፍይ በሆነ አመለካከት እንዲጠመዱ በማድረግና ባስተማሪዎችና በተማሪዎች የሚነሱትን ተራማጅ ጥያቄዎች በመጨፈለቅ ከፖለቲካዊ ወገናዊነት ነፃ የሆነና ብቃት ያለው ዜጋ የሚያንፅ የትምህርት ፖሊሲ እንዲረጋገጥ ከማስቻል ይልቅ እንደለመዱት የማደናገር እንቅስቃሴያቸውን በመቀጠል በምርጫው ዋዜማ ላይ ህዝቡን እየሰበሰቡ በማይጨው፤ ደባርቅና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ዩኒቨርሲቲዎች ይገነባሉ፤ ሌላም ሌላም ብለው መቀባጠራቸው ሆን ብለው ህዝቡን ለማታለልና ለማዘናጋት ካልሆነ በስተቀር መሰረታዊ የህዝቡን ጥቅም ለማረጋገጥ አስበው እንዳልሆኑ መታወቅ ይገባዋል።
    የሚያስገርመው ነገር ቢኖር ያገራችን የትምህርት ስርዓት ባስከፊ ገፅታ ላይ እያለና ጤነኛ ዜጋ ማፍራት ያልቻለና ትውልድ ገዳይ ሆኖ እየቀጠለ ባለበት ባሁኑ ግዜ ይሰራል እያሉ የሚናገሩበትና እንደ መንግስት ግዴታቸውና ሃላፊነታቸው እንደሆነ አምነው መስራት እንደሚገባቸው ረስተው በዓላት በሚከበሩበትና ምርጫዎች ለማካሄድ በሚዘጋጁበት ዋዜማ ላይ ለቅስቀሳ ስራ ሊያውሉት መሞከራቸው አገራችን ውስጥ ያለው ስርዓት ምን ያህል ህዝባዊ ሃላፊነት እንደሌለውና ርካሽ መንግስት እንደሆነ የሚያሳይ ገፅታ  ነው።
     የህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች ከኛ በላይ ትግራይ ውስጥ ሊፈጠር የሚችል ሃይል የለም እያሉ ህዝቡን እየቀሰቀሱት ባሉበት ባሁኑ ግዜ የየካቲት 11 ክህደት የወለዳቸው በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰፊና ረጅም አስተሳሰብ ያላቸው ድርጅቶች እየታገሉ ይገኛሉ።
    የነዚህ ድርጅቶች ትግል ከግዜ ወደ ግዜ በሁሉም መልክ እየተጠናከረ ባለበት ግዜ ዛሬ ለማስመሰል ብለው 24 ዓመታት ሙሉ የት አለህ ብለውት የማያውቁት ጀግኖች ሰማእታት የወደቁባቸው ቦታዎች እየፈለጉና መቃብራቸው ወዳለበት ቦታ መንቀሳቀሳቸው ያለፉትን ሰማእታት ለመዘከር ሳይሆን ተቆርቋሪዎች መስለው የስልጣን እድሜአቸው ለማራዘም ብለው ያደረጉት ተራ እንቅስቃሴ ነው።
     ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ግን በ17 ዓመት የትግል ወቅት የተከፈለውን ከ60 ሺህ በላይ ህይወት በ 40ኛው የህወሃት ልደት በዓል ላይ 40 የሚያህሉ የሰማእታት አስከሬን ለስድሳ ሺውን ሰማእታት ወክለው ወደ ሰማእታት ሃወልት እንዲያርፉ አድርገናልና ያገሬው ህዝብ እወቅልን ማለታቸው ነው።
    እስካሁን የት ነበራችሁ? ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተገኘ? አሁን ላይ ደርሳችሁ የሰማእታትን አስከሬን ማፈላለጋችሁ ለምን አላማ ተብሎ? ነገሩ! ጉዳት ከመድረሱ በኃላ ምክር መለገስ ለሞተ ሰው መድሃኒት እንደመስጠት ይቆጠራል ነውና ህዝቡ በስርአቱ ሰይጣናዊ ቅስቀሳ ተደናግሮ ለማስመሰል ተብሎ እንዲካሄድ በተዘጋጀው ምርጫ ላይ ከመሳተፍ መታቀብ ይገባዋል።