Saturday, May 28, 2016

ግንቦት 20ን ምክንያት በማድረግ ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ!



የታላቅ ታሪክ ባለቤት የሆንኸው ክቡር ታጋይ ህዝባችን ሆይ፥ በላይህ ላይ ይወርድ የነበረውን የመሳፍንታዊና የፋሽስታዊ ስርዓቶች ግፍ ገርስሰህ፣ ክብርትና ሉዓላዊት በሆነችው አገርህ ኢትዮጵያ፣ ህዝባዊ ስርዓት አቁመህ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችህን ልታስከብር፣ ለ17 ዓመታት ያካሄድኸው መራራ ደማዊ ጦርነት አልፈህ የግንቦት 20ን ድል ከጨበጥህ ይኸው ድፍን 25 ዓመታት ተቆጥሯል።
    የደርግን ፋሽስታዊ ስርዓት ለመገርሰስ ያነሳኸውን የትጥቅ ትግል ለድል ለማብቃት ደግሞ ትግሉ የጠየቀውን ሁሉ ከአነስተኛ እስከ መተኪያ የማይገኝላት ክብርት ህይወትህ አበርክተህ ዓለም ለማመን የከበዳት እጅግ ድማቅ ታሪክ ሰርተሃል፣በዚህ መራራና ውጣ ውረድ የ17 ዓመት የትጥቅ ትግልህ ውስጥ ከ60ሺህ በላይ ብሩክ ልጆችህን ገብረሃል፣ ከ100ሺህ በላይ ለአካለ ጎደሎነት የከፈልኸው የትናንትና ታሪክህ ነው።
   ይህ ከባድ መስዋዕትና ስንክልና የተከፈለበት ዋነኛ ዓላማ ከግንቦት 20 ድል በኋላ በመላ የአገራችን አካባቢዎች የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ህገመንግስታዊ ዋስትና አግኝተው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተከብሮ ።ተፈጥሮአዊ አደጋ ድርቅና ጦርነት በላይቸው ላይ የሚያሳድረው ሰቆቃና ድህነት ተገፎ ።ከስደት የሚያላቅቅ የተመቻቸ አስተዳደር በማስፈን ፣ከአገራቸው ፀጋ እኩል ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ፣በሰላም ተከባብረው የሚኖሩባት ህዝባዊ መንግስት የተቋቋመባት ።አንዲት የበለፀገች ዴሞክራሲያዊትኢትዮጵያን   ለመገንባት ነበር።
    ይሁን እንጂ ህዝባዊ ትግልህ በጥቂት ከሃዲዎች የህወሃት ኢህአዴግ አመራሮች ተገፈፈ። የታግልክበትን ዓላማ ወደጎን በመተው በግል ኑሯቸውና ሙስና በመዘፈቅ ወደ ከፋ ጎስቁልና ድህነትና ስደት አጋልጠውሃል፣ ብቻ ሳይሆን ዛሬ በልጆችህ መስዋዕትና ስንክልና ያገኘሃትን መሬት ነፃ ሆነህ እንዳትረግጣት ፤መብትህን እንዳትጠይቅ፤እንዳትደራጅ ፤እንዳትቃወም በልጆችህ መስዋዕት ላይ እሾህ እንጥፈው ከሚመሩህ ሩብ ክፍለ ዘመን ሆኖሃል።
    በእነዚህ ተቆጥረው ባሉ የአፈና ዓመታት ህወሃት ኢህአዴግ በመላ ሃገር ለዴሞክራሲ የሚያፍን ሰንሰለት በመዘርጋት በፀጥታ ኃይሎች በአደባባይ ተጠያቂ በሌለበት ልጆችህ ህይወታቸው ሲቀጠፉ በስውርና በገሃድ እየታፈኑ አድራሻቸው ሲጠፉ እንዲሁም ባልፈፀሙት ወንጀል በጥላሸት ክስ እስርቤት በመግባት ለዓመታት ሲማቅቁ ማየት ዕለታዊ ፍፃሜ ሆኖአል።
    የተከበርከው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ። ለፍትህ፤ለሰላም፤ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ለማግኘት የከፈልከው ሁለጎናዊ መስዋዕትና ስንክልና በግላዊ ጥቅም ፈላጊዎች የህወሃት ኢህአዴግ ስግብግብ መሪዎች እጅ ስር ወደቀ፣ፍትህ ለማግኘት ገንዘብ እየተጠየቅህ፤ፈጣን አገልግሎትና ምቹ አስተዳደር አጥተህ። ላይና ታች ስትንገላታ ወደከፋ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አጋልጦሃል፣መሬት ላይ በተግባር በማይታየው በውሸት መረጃ ሲያደናግርህ የቆየው እድገትህና የአገርህ እድገትም ቢሆን በዚህ አመት ባጋጠመው የድርቅ አደጋ ተከትሎ እየተከሰተ ባለው የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ በየቀኑ እየጠፋ ላለው የዜጎች ህይወት ለመታደግ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ የማያስችለው የቃላት እድገት መሆኑ ሽፋኑ ተገልጧል።
    የተከበርኸው የአገራችን ወጣት፦  የዚህች አገር የእድገትና የለውጥ  መሰረት ወጣቱ ቢሆንም እንኳ ያሉህ እድሎችና መጭው ራዕይህ በህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች እየጨለመ ነፃነትህንና መብትህን ታፍነህ እውነቱን በማጋለጥህና ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችህን በመጠየቅህ ባልዋልከው ወንጀል ስትጠየቅና በጠላትነት ዓይን እንድትታይ ተፈርዶብሃል ብቻ ሳይሆን በስራ አጥነትህ ተቸግረህ ተገቢ የመሬት ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ተነፍጎህ እንዲሁም የእለት ጉርሱን ይቅርብኝ ብሎ ሳይማር  ያስተማረህን ድሃ ቤተሰብህን ውለታውን እንዳትከፍለው ህይወትህን አደጋውስጥ አስገብቶት ይገኛል።
    ይህ በመሆኑ ነው ሳትወድ በግድ ተገድህ አገርህን ጥለህ ወደ ባዕድ አገር እየተሰደድህ ማለቂያ የሌለው ስቃይና አሰቃቂ የሆነ ግድያና አስከፊ መከራ የሚወርድብህ ። ስለዚህ ስደት የተጨቋኝነትህ መፍትሄ ሊሆን ስለማይችል ለዚህ በላይህ ላይና በሌሎች ወገኖችህ ላይ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እያካሄደ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም እየጨፈለቀህ ያለው የፌደራል ፖሊስ ፤አጋዚ ኮማንዶና ልዩ ኃይል በመላክ ሰላምና ደስታህን አሳጥቶህ ያለውን  ስርዓት በአንፃሩ ተሰልፈህ ሁለጎናዊ ትግልህን በማጠናከር  በቃህ እንድትለው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን )ጥሪውን ያቀርብልሃል።
    የስርዓቱ ታጣቂ ኃይሎች፦ ኢህአዴግ የስልጣን እድሜውን ለማስረዘም እየተጠቀመበት ያለው ዘዴ እንቢ ብሎ ለአመፀ ህዝብ በጠመንጃ አፈሙዝ በመጨፍጨፍ በፍርሃት እንዲያድር በማድረግ ነው። የዚህ ዋነኛ ተግባሪና መሳሪያ አድርጎ የሚጠቀምባችሁ ደግሞ ከህዝብ ጉያ ለወጣችሁ ታጣቂ ሰራዊት ነው። እናንተ መጀመሪያ ስትታጠቁ አገራችሁን ከጠላት ልትከላከሉና ህገመንግስቱን ልታስከብሩ ነው እንጂ የስርዓቱ ከዳም በመሆን ህዝብ ልትጨፈጭፉ አይደለም የታጠቃችሁ።
     ስለዚህ ኗሪ ህዝብ እንጂ ኗሪ ስርዓት እንደሌለ አውቃችሁ ይህ ስርዓት ነገ በህዝብ ትግል ሲወድቅ የታሪክ ተጠያቂ ከመሆን፣ ጊዜው ሳይሄድባችሁ ከህዝባችሁ ጋር እንድትወግኑና ታጥቃችሁት ያለውን ጠመንጃ በህዝብ ላይ ከማነጣጠር ወደስርዓቱ እንድታዞሩና ለለውጥ እየተካሄደ ላለው ትግል ተሳታፊ እንድትሆኑ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ጥሪውን ያቀርብላችኋል።
 የተከበራችሁ ሁሉን ዓይነት ትግል እያካሄዳችሁ ላላችሁ ተቃዋሚ ድርጅቶች፦
   ይህ ሩብ ክፍለ ዘመን አስቆጥሮ ያለው ስርዓት እስካሁን ሊቆይ የቻለበትን ምክንያት ልትፈትሹ ይገባል። ወያኔ ኢህአዴግ ስረ-መሰረቱ የተነቃነቀና የተቦረቦረ በህዝብ ዘንድ ቦታ የሌለው ስርዓት ነው።እስካሁን በስልጣን ሊያስቆየው የቻለ ምክንያት ግን የእኛ የተቃዋሚ ድርጅቶች ድክመት ነው ብለን እናምናለን።
    ትግላችን ከስርዓቱ ጋር ያነጣጠረ መሆን እያለበት አንዳንድ ድርጅቶች የፖለቲካ ብስለት ከጎደለው አመለካከት የተነሳ የአንድ ብሄርን ነጥለን የስርዓቱ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርገን ስለምናየውና እየታገልንበት ያለውን ትርጉም ስተን ብሄሩን ስንሳደብ ስለምንውል ህዝቡ ሳይወድ ከስርዓቱ ጋር እንዲጠጋ እያደረግነው ነው።
    በሌላ በኩል ሁሉን አይነት ትግል እያካሄድነ ያለን ድርጅቶች በሃቅ ለውጥ የምንፈልግ ከሆነ በአንድ ግንባር ልንሰምርና ልንወሃሃድ አንድ ልንሆን አልቻልንም። አስከፊ ችግርና ስቃይ እያሳለፈ ያለውን ህዝባችንን ልንታደገው ከሆነና በአገራችን  ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲተከል የምንፈልግ ከሆነ መጀመሪያ ይህ ጥያቄ ሊመለስ ይገባዋል። ቴክኖሎጂ በወለዳቸው የመገናኛ ብዙሃን ተንጠልጥለን መፎከር ብቻ በቂ አይደለም።
     ለማጠቃለል የዘንድሮው ግንቦት 20 ከአለፉት ዓመታት ሁሉ በከፋ መልኩ የመልካም አስተዳደር ሰንሰለት በተበጠሰበት ፤ሙስና በነገሰበት ፤ዜጎቻችን ከውስጥና ከውጭ በሚመጡ ርህራሄ በሌላቸው ታጣቂዎች እየተጨፈጨፉ ባሉበት ፣ የመብት ጥያቄ ያስነሳው ህዝባዊ ዓመፅ እየተቀጣጠለ ባለበት ወቅት ሆነን ነው እያሳለፍን ያለነው።
   ስለዚህ በውስጥም በውጭም የምትገኝ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ  ፀረ ህዝብ ከሆነው ከኢህአዴግ ስርዓት አንፃር ሳትሰለች እያደርግከው ያለህው ሁለጎናዊ ትግል ግዴታህና ኃላፊነትህ ነውና አጠናክረህ ልትቀጥለውና ወደአንድ የለውጥ ነጥብ መደምደሚያ እንድታበቃው እያሳሰበ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ዘወትር ከጎንህ ይቆማል።
የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን)
ግንቦት 20 2008ዓ.ም
ድል ለጭቁኖች!!

No comments:

Post a Comment