Tuesday, June 21, 2016

ሰኔ 15 የሰማእታት ቀንን ምክንያት በማድረግ ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ፥



   ህዝባችን በ1967 ዓ.ም እስከ አፍንጫው ዘመናዊ መሳርያ የታጠቀ የደርግ አምባገነን ስርአትን በመቃወም የትጥቅ ትግሉን ሲያስነሳ ጦርነት የህወትና የንብረት ዉድመት እንደሚያስከትል ስለጠፋው አልነበረም። የነበረው ስርአት በትግሉ ጊዜ ከጠፋው ህይወት በላይ እያጠፋ ስለ ነበረ ለተወሰኑ አመታት መስዋእት በመክፈል ለዘላአለም በሰላም መኖር ይሻላል ከሚል ተስፋ ተነስቶ ነው የትጥቅ ትግሉን ትግሉን የጀመረው።
   ያነሳዉን አላማ ወደ ተግባር ለመቀየር ደግሞ ለ17 ዓመታትን ሙሉ በሚያስደንቅ ፅናትና ጀግንነት ያካሄደው ደማዊ ጦርነት ከነፍስ ወከፍ የትግራይ ቤቶች የተመረጡ ወጣቶች ህይወት ተከፍለዋል፣ ህዝባችን ከንብረቱ እስከ መተኪያ የሌላት ህወቱንና የልጆቹን ህይወት ለተካሄደው የአፈሙዝ ትግል አበርክቷል።

    በአፍሪካ ምድር በሃያልነቱ የሚታመንበትና ሊገፋ የማይችል ተራራ ነው ተብሎ ይገለፅ የነበረዉን የደርግን ፋሽስታዊ ስርአት የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ ሲጥለው፣ በአስፓልት መንገድ እየተጓዘ ሳይሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የተመረጡ የህዝብ ልጆችን በመክፈል ነው።

   ህዝባችን መራራ ትግልን ያሳለፍውና፣ ሙሉ በሙሉ ተነስቶ መስዋእትነት ለመክፍል የተቀዳደመው የመስውእት መራራነት ስለጣፈጠው ሳይሆን፣ ከመስዋእትነቱ በኋላ ሰላም። ፍትሕ። የተሟላ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ወዘተ ሳይሸራረፍ በሃገራችን እንዲነግስና ህዝብ እንዲጠቀምባቸው ከሚል አላማ ተነስቶ ነው።

    ቢሆንም ግን የህወሓት ከዳተኛ አመራሮች ለዚህ እየተካሄደ  ለነበረው ትግል ልጆቹን መርቆ ለመስዋእትነት  ያሰለፈ።  ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እስከ መጨረሻ ተቋቁሞ የደርግን ስርአት የገረሰሰ ጀግና ህዝብ በመካድ ወደ ግላዊ ኑሯቸውና ሙስና ተዘፍቀዋል ብቻ ሳይሆን ትናንትና በነበረው ትግል ህይወቱን የሰዋ ታጋይም በሚገባ ታሪኩ ተሰንዶ ለቤተሰቡ በአገባቡ እንዲረዱ አልተደረገም፣

    እነዚህ  በትግሉ ወቅት ያልተገደበ የማይተገበር ቃል እየገቡና እየማሉ የነበሩ የህወሓት መሪዎች የትግሉን አላማ ተግባራዊ በማድረግ የህዝብን ጥያቄ ሊመልሱ። ዴሞክራስያዊ አሰራር ሊያስፍኑ ይቅርና በሙስናና ግለኝነት ተግባር  ተዘፍቀው ለዚህ መራራ ትግል ያሳለፈ ህዝባችንን ወደ ከፋ ጥፋትና ዉድመት አጋልጠዉት ይገኛሉ።

   የተከበርክ ጀግና ታጋይ ህዝባችን፣ በላይህ ላይ እየወረደ ከነበረዉ የደርግ ኢሰፓ ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ ለመገላገል ስትል ለ17 አመታት ከዘመናዊ መሳርያና አእላፍ ሰራዊት በመግጠም ባሳየኸው ተነሳሽነትና ፅናት ደርግ የሚባል ስርአት ከስረ መሰረቱ ነቅለህ ለመጣል ብትችልም፣ ከአብራክህ የወጡና ያሳደካቸው መሪዎች መሰዋእትነትህ ብላሽ ሆኖ እንዲቀር ማድረጋቸው ሳይበቃ በስምህ እያላገጡ ወደ አልጠበቅከው ጭቆናና መከራ እየመሩህ ይገኛሉ።

   የህወሓት መሪዎች ትናንትና የት እንደወደቁ ያማያዉቋቸውን ልጆችህ በየአመቱ የሰማእታት ቀን ምክንያት በማድረግ በበአሉ ስም ከቃል የማያልፍ የተለመደ መግለጫና መዝሙር ከሚያሰሙህ ሩብ ዘመን አስቆጠረዋል።የልጆችህ መስዋእትነት ግን ተኝቶ ጊዜ እያሳለፈ ቆይቶ በሰማእታት ቀን ስም ቃላቸው እናክብራለን ብሎ ሻማ በመለኮስ የሚደሰኩር ስርአት ለመትከል አልነበረም፣

   የልጆችህ መሰዋእትነት በህዝብ ላይ የሚወርድ ጭቆናና ግርፋት እንድያበቃ፣ ህገ መንግስት ዋስትና እንዲያገኝ፣ የህግ የበላይነት ተከብሮ ሰላም እንዲሰፍን፣ ፍትሕ እንዲነግስ፣ ህዝብ ዴሞክራስያዊና ሰብአዊ መብቶቹ በሚገባ ተጠብቆለት የመሰለውን አስተያየትና አመለካከት እንድይዝና እንዲደግፍ፣ ወደ ፈለገው የአገሩ አከባቢዎች ተንቀሳቅሶ እንዲሰራ የሚያስችለው መንገድ እንዲመቻችለትና ለተግባራዊነቱ የሚታገልና የሚከታተል ስርአት ለማስፈን ነበር ፍላጎቱ።

   ይሁን እንጂ በህዝብ ልጆች መስዋእትነት ተጠቅመው  ለስልጣን የበቁት የተወሰኑ የህወሓት መሪዎች የስልጣናቸውን ዕድሜ በሚያራዝም መንገድ የተከተሉት የዉድመት ፖሊሲ ኢትዮጵያዉያን አንድነታቸውን በታትኖ በመጥፎ አይን እንዲተያዩና በተለይ ደግሞ ከመጥፎ  መሪዎች ጥላቻ የሚነሳ ሌሎች ቢሄሮች ለትግራይ ህዝብ አሉታዊ አመለካከት ሲያሳዱሩበት እየታዘብንና እየተመለከትን እንገኛለን።
   ህወሓት ግን ለትግራይ ህዝብ እንደማይወክለው የሚታወቅ ሆኖ ከመጀመርያ ጀምሮ በክዳት መልሶለታል፣ስለዚህ አሁንም የትግራይ ህዝብ ማለት ህወሓት፣ ህወሓት ማለት የትግራይ ህዝብ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው የሚል የአንድ አንድ ሰዎች የተሳሳተ አመለካከት ጊዜ ሳይወስድ በቀናነት  የእርምት  እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ የደከመ አስተሳሰብ ነው፣ ምክንያቱ የትግራይ ህዝብና የህወሓት ድርጅት የሰማይና የመሬት ያህል ልዩነት ያላቸው ሁለት ተቃራኒ ሃይሎች በመሆናቸው።

    ህወሓት ማለት የትግራይ ህዝብ ቢሆን ኑሮ የትግራይ ህዝብ በከፈለው መስዋእትነት ተጠቃሚ ቢሆን ይህ በትህዴን እየትካሄደ ያለው በህወሓት ኢህአዴግ ላይ ያነጣጠረ በትግራይ ተወላጆች የተመሰረተ ትግል ለምን አስፈለገ ይሚል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያስተዉልበት ይገባል።ምክንያቱ በህወሓትና በትግራይ ህዝብ ያለው ልዩነት የሚያሳየን በቂ መረጃ በመሆኑ።
   የህወሓት መሪዎች ግን አሁንም በመጨረሻ ዉድቀታቸዉ ባሉበት ወቅት ከ25 ዓመታት በኋላ የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል ታሪክ መሰነድ አለበት በሚል ኑዛዜ በመግባት የህዝብ ገንዘብ ሰብስበው በህዝብ ልጆች እየቀለዱ ባሉበት ወቅት አቁሙ እንድትላቸው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ጥሪዉን ያቀርባል፣

    ክብርና ሞጎስ ለሰማእቶቻችን
  የትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ (ትህዴን)
                            ሰኔ 15 2008 ዓ.ም


No comments:

Post a Comment