Thursday, November 17, 2016

ጭቆና የወለደው ህዝባዊ ትግል፣በአፈና ሊገታ አይችልምየኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት በአገር በቀል ጨቋኝና በዝባዥ መንግስታት በባርነት ሲገዛ ቆይቷል። ነፃነት፤እኩልነት፤ፍትህና ሰላምን ሳያገኝ በተጨቋኝነት ቀንበር ስር መከራና ስቃይ እየተፈራረቁበት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ተነጥቆ በድህነትና በኋላቀርነት ተዘፍቆ በማህበራዊ፤በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ሲዋኝ ቆይቷል።

ከእነዚህ አስከፊ አገዛዞች ለመላቀቅ በተደጋጋሚ ጠንካራ ትግሎችን እያደረገ መጥቷል። የንጉሳዊ አስተዳደርን በህዝባዊ ዓመፅ በአብዮቱ አስወግዷል። የአምባገነኑን ወታደራዊ አገዛዝም ዓመታትን በፈጀና ብዙ ህይወትን ባስከፈለ የትጥቅ ትግል አስወግዷል። ይሁን እንጂ መላ የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደየድርሻቸው  በከፈሉት ከባድ መስዋዕትና ጀግንነት ተሽቀዳድሞ ወደስልጣን የመጣው ወያኔ ኢህአዴግ መንበረ ስልጣኑን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ ተግባረ ቢስ የሆኑ የማይጨበጡና ተስፋ የለሽ ቃል ኪዳኖችን በመዝራት የከፋ አምባገነናዊ ስርዓት ወያኔ ኢህአዴግ ተተክቷል።

እውነታው ግን ወያኔ ኢህአዴግ ካለፉት መንግስታት በባሰ ሁኔታ ጨቋኝ ስርዓት በመሆኑ በወገኖቹ ላይ ለ25 ዓመታት ሙሉ በግልጽና በድብቅ እያወረዳቸው የመጣውና እያደረጋቸው ያለው አይን የለኝ ጥርስ የለኝ ጭፍጨፋዎች፤እስራቶችና እገታዎች ቢፈተሹ እውነታው በግልጽ ይታያል።     

የኢትዮጵያ ህዝብ ከገዥዎች የጭቆና ቀንበርና ግርፋት ያልተላቀቀ ህዝብ እንደመሆኑ መጠን፣ ፀረ ህዝቡ የወያኔ ኢህአዴግ ጉጅሌ ከመጀመሪያ ጀምሮ በፈጠራቸው መሰረታዊ ስህተቶችና አፈናዎች በሰላማዊ መንገድ በመጠየቅ መፍትሄ በመፈለግ ባደረገው ጥረትና እንቅስቃሴ፣ በጠላት አይን እየታየ አውዳሚ፤ፀረ ሰላም፤ፀረ ህገመንግስት የሚል መልስ እየተሰጠውና ከዚህ ባለፈም በስውር ታግቶ እየተወሰደ እየጠፋና በእስርቤት ለአመታት እንዲሰቃይ ተፈርዶበታል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አመፀኞችንና ረጋጮችን እንዴት አድርጎ እንደሚያስወግዳቸው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በላዩ ላይ በሚወርደው ግፍና ብዝበዛ ሳይዳከም ለሩብ ክ/ዘመን ሙሉ በተለያየ መንገድ በአገር ውስጥም ይሁን       በውጭ ተደራጅቶ ሰላማዊ ትግልም ይሁን የትጥቅ ትግል እያካሄደ ለሩብ ክ/ዘመን ያክል ስልጣን ለግሉ አድርጎ የህዝቡን ደም እየመጠጠ ለመኖር እየተስገበገበ ላለው ጨቋኝ የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት የመጨረሻ ፍርዱን ለመስጠት ከሞቱ አፋፍ ስር አድርሶታል።
ይህ በመሆኑ ደግሞ ዛሬ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተጨቋኝነትና በደል የወለደው ህዝባዊ አመፅ ተቀጣጥሎ በመነሳቱ ፣ወያኔ ኢህአዴግ ዘላቂነት ያለው ሰላምና ፍትህ ከማፈላለግ ይልቅ በአፈና ተግባርና የተለያዩ የማደናገሪያ ተግባራትን ለመቀመር ሲሽሎከሎክ ይታያል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በውስጣዊ ችግሩ የተፈጠረውን ሁከትና ብጥብጥ በውጭ ሃይሎች የተፈጠረ እንደሆነ አስመስሎ አዳዲስ ድራማዎችን እየፈለሰፈ አንደኛውን አሸባሪ ሌለኛውን ወራሪ በሚል ስም ሲጠቀምና፣ በሌላ በኩል ደግሞ አይኑን ባወጣ የማታለያ ሴራ ወያኔ ኢህአዴግ በጥልቀት ታድሷል በሚል ከላይ እስከ ቀበሌ ያለው አስተዳደራዊ መዋቅር በየደረጃው መፍትሄ የሌለው ግምገማ እያደረገ ይገኛል።

ህዝቡ ግን የወያኔ ኢህአዴግን አፈናና የማደናገሪያ ስልቶቹን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ትንፍሽ እንዳይል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም የታገደውን ሁለንተናዊ መብቱ እንዲሁም በፀጥታ ሃይሎች በየቀኑ እየደረሰበት ያለው እስራትና ግድያ ሳያንበረክከው ሲያካሂደው የቆየውን ትግልና አመፅ እየጠነከረ ቀጠለ እንጂ  በወያኔ ሴራ ሲደናቀፍ አልታየም።

እንዲያውም በወያኔ ጉጅሌ እየተካሄዱ ያሉትን የተለመዱ የማደናገሪያ ተግባራት አያስፈልገንም፣ይህ ሰላማዊ መፍትሄ አይደለም።ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የጠየቀ ህዝብ በአፈና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተጥሷል። ህዝብ እየታሰረና እየተጨፈለቀ ሰላሙ እየታወከ አይደለም መፍትሄው። በመሰረቱም ህዝባዊ ስልጣን በጥቂቶች የሚለካ ወይም የሚታደል ሳይሆን ሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎና መነቃቃት የሚያስፈልገው ጉዳይ በመሆኑ ህዝብን ረግጦ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የለም በማለት ይገኛል።

ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን እንዲከበሩለት የጠየቀ ህዝብ እጣው እስራትና ግርፋት ከሆነ በትግሉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እያካሄደው ያለው ህዝባዊ አመፅ በአፈናና በማደናገሪያ ዘዴዎች ሳይገታ፣ ነበልባል እየጨመረ እየተቀጣጠለ በመሄድ ላይ ስለሆነ ህዝባዊ ጥያቄ ያስነሳው ዓመፅ በኃይል እርምጃ ሊገታ አይችልም።

No comments:

Post a Comment