Monday, January 2, 2017

የጨለማ ተሃድሶህዝባችን ሰላም አግኝቶ የፍትህ ተጠቃሚና የስልጣን ባለቤት የሚሆንበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ሲል ህዝባዊነት የሌላቸውን ጨቋኝ ስርዓቶች በክንዱ ድባቅ እየመታቸው እንደመጣ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው።
ሆኖም ግን “ባጎረስኩ እጀን ተነከስኩ” እንደሚባለው የአበው አባባል ሆኖ በመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል መስዋዕት፣ ስልጣን ጨብጦ ያለው የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት፣ ከአለፉት ስርዓቶች አምባገነንነትን ወርሶ የህዝብ ስልጣንን ለብቻው በማድረግ፣ በገዛ ደሙ ወደስልጣን ባወጣው ህዝብ ላይ በየቀኑ ለመገመት የሚያስቸግር ግፍና በደል እያወረደ ይገኛል። ይህ አምባገነን ስርዓት በህዝብ ላይ ለሚፈፅመው በደል ለማረም የሚሰጠውን ምክር ባለመቀበሉ ወደባሰ ሁከትና ግርግር እንዳመራ የሚታወቅ ነው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉንም አይነት አማራጮች ሞክሮ ምላሽና ፍትህ በማጣቱ እንደቀድሞው በትግሉ የስርዓት ለውጥ ለማድረግ በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ህዝባዊ ዓመፅ ተቀጣጥሎ ይገኛል።
ይህንን ተከትሎም የኢህአዴግ ባለስልጣናት የስርዓት ለውጥ ለማምጣት በማቀጣጠል ላይ ያለውን ህዝባዊ አመፅ አቅጣጫውን ለማሳት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ወደለየለት ወታደራዊ ትዕዛዝ ገብቷል። በንፁሃን ዜጎች ላይ እያካሄደው ያለው አፈናና ግፍ፣ በተለይ ደግሞ የአማራና የኦሮሞ ወጣቶችን ከአደባባይ እያፈሰ ወደ እስርቤቶችና ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች እንዲወርዱ ፈርዶባቸዋል።
በተለይ ወደ ብርሸለቆ፤ ጦላይ፤ ይርጋለም፤ አዋሽ ዘጠኝና ሌሎችም ማሰልጠኛዎች የአገራችን ወጣቶች ስለመብታቸውና ተጠቃሚነታቸው ስለጠየቁና ስለተቃወሙ ብቻ በስርዓቱ የፀጥታ ሃይሎች ተደብድበዋል።  በጥይት ተረሽነዋል። በእነዚህ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እስርቤቶች ምንም አይነት ወንጀል የሌለው ንፁህ ወገን በጥርጣሬና በስጋት ብቻ በፀጥታ ሃይሎች ከቤቱ ውስጥና ከጎዳናዎች እየታፈሰ ለእስር በመዳረግ በረሃብና በጥማት ብሎም አሰቃቂ የወንጀል ምርመራ ቶርቸር አስገብቶ በማሰቃየት ያልዋሉበትን ድርጊት ወንጀለኛ ነኝ፣ አይደገምም በል እየተባሉ የሚሰቃዩት ዜጎች መቁጠሪያ የላቸውም።

በዚህ መሰረት ይህ ፀረ ህዝብ ቡድን መብቴን ያለውን ህዝብ በቁጥጥር ውስጥ እያስገባ፣ እናንተ መብት የሚባል ነገር አያስፈልጋችሁም። የሆነ አይነት ጥያቄ ካነሳችሁ እጣችሁ ይህ ነው እያለ አረመኔያዊ ተግባር እየፈፀመ አስገድዶ በማናዘዝ ከዚህ ከወጣችሁ በኋላ ደግሞ ወደሁከትና ግርግር አልመለስም፣ አልገባም ብላችሁ መሃላ ፈፅሙ እያለ የተወሰኑትን ትርጉም የሌለው የአፈና ታርጋ ለጥፎ ሲለቃቸው አብዛኞች ደግሞ በስቃይና በመከራ ስር ሆነው እጣቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
በዚህ ሁኔት በስጋት ተውጦ ያለው የስርዓቱ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለመብታቸውና ለተጠቃሚነታቸው ሲሉ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ተገደው ወደ አደባባይ በመውጣት የተቃወሙትን ዜጎች ዓመፅ አንስታችኋል እየተባሉ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ወርደው ለብዙ ወራት ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ፣ ሰሞኑን “አይደገምም” የሚል ምልክት ያለው ጨርቅ በማልበስ የተለመደውን ተግባረቢስ ፕሮፖጋንዳ ሲናገርና ሲሰብክ ታይቷል።
ከእነዚህ አስመሳይ ቃላቱ ውስጥ የተወሰኑትን ለመግለፅ ያክል መንግስት የራሱ ችግሮች ያሉት መሆኑን በማመን እነዚህን ስህተቶች ለማረም ደግሞ በተሃድሶአችን ታርመናል፣ እናንተም የተሃድሶ ስልጠና ወስዳችኋል የሚል መማፀኛ ቢያሰማም እንኳ ይህንን ተግባር ግን ብዙ የፖለቲካ ተንታኞችና ምሁራን “ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ” የተደረገው ተሃድሶም የጨለማ መንገድ ነው ብለውታል።
ምክንያቱም የወያኔ ኢህአዴግ አመራሮች ከመሃላና ከቃልኪዳን ባለፈ ከአረመኔያዊ ተግባራቸውና ከስልጣን ስስታቸው ተቆጥበው ለህዝብና ለሃገር የሚቆረቆር ህሊናና ህዝባዊ ወገንተኝነት ተሰምቷቸው በተግባር ሊሰሩና ሃገርን ከመበታተንና ከድህነት እንደማያድኑ ህዝብ በደንብ ያውቃቸዋል። ስለዚህ አሁንም ቢሆን ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በህዝብ ላይ እያደረሰው ያለው ግፍና በደል እንዲያበቃና በሌላ በኩል ደግሞ ስርአቱ እያደረገው ያለው ወደ ጨለማ የሚያስገባ ተሃድሶ እንዲያከትም ሁሉም የበኩሉን ሊያደርግ ይገባል። ምክንያቱም መብታችን ይከበር ብሎ የጠየቀ ጭቁን ወገን ወደ አረንቋና ወታደራዊ ማሰልጠኛ እስርቤቶች ታጉሮ የጨለማ የተሃድሶ መንገድ ስለሚፈረድበት።


No comments:

Post a Comment