Sunday, August 27, 2017

የትግራይ አካባቢ ጥበቃ በህዝብና በውጭ አካላት እንዴት ሰርቷል?



   የአሸንዳን በዓል ወይም ደግሞ የማርያን በዓል ተጠቅሞ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ የተሰጠውን ድራማዊ መግለጫ የሚመለክት ሆኖ፣እለቱን ተዘጋጅቶ በመጠበቅ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት በሚል ትግራይ በቻይና በተካሄደው አካባቢን የማዳን ዘመቻ በሚመለከት የወርቅ ተሸላሚ ናት ብለውናልና የትግራይ ህዝብ እንኳን ደስ አለህ! በማለት እንደ አንድ ታላቅ ብስራትና ስጦታ ይዞ እንደመጣ ሲገልፅ ታይቷል።
   ብዙ ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ወይም በሚዲያ የሚከታተልባቸውን በዓላት በመጠቀም መሬት ላይ በተግባር ለሌሉት ተግባሮች በየመድረኮች ግን በተስፋ የሚያንጠለጥልሉ ጣፋች ልሳናትና መግለጫዎችን መስጠት የወያኔ ህወሃት የተለመዱ ተግባሮች ናቸው።
   የዚህ ማስቀጠያም ነው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አባይ ወልዱ ትግራይ የአካባቢ ጥበቃ ምርጥ ተሸላሚ ተብለናል በማለት በዚህ በብዛት በአካልና በቴሌቪዥን በሚከታተለው ደማቅ የአሸንዳ በአል ተገኝቶ እንኳን ደስ አለን ሲል የታየው።
   ይህ ጉዳይ በሚገባ ተፈትሾ የረጅም አመታት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የትግራይን አካባቢ የማዳን ዘመቻ ጥናት ተደርጎበት ውጤት ያለው ስራ ከተገኘ ልክ ወያኔ ህወሃቶች እንደሚሉት እንኳን ባይባል ለቀጣይ በርትቶ ለመስራት የሚገፋፋ ነው።
   ግን የትኛው የትግራይ አካባቢ ነው ምርጥ ተሸላሚ ሊያስብላት የቻለ? ትግራይ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት በምን ሁኔታ ላይ አለች? እነዚህ መመዘኛ ደረጃዎችስ በትክክል ለትግራይ የሚገልፁና ውጤት ያለው ስራ የታየባቸው መለኪያዎች ናቸው? በትግራይ ላለው የወደመና የተጎሳቆለ አካባቢ በየትኛው አይን ታይቶና ተፈትሾ ነው ለዚህ መድረክ ሽልማት የተደረሰው? እነዚህን መለኪያዎችስ ህዝብ ያምንባቸዋል ወይስ ጥቂቶች በወረቀት አስፍረው ባወጡት ይሁን ተብሎ የተሰራ ጨዋታ ነው? ወዘተ ተብሎ ጥያቄ ለማንሳት ያስገድዳል።
   መልሱ ደግሞ ለቀባሪ ማርዳት እንዳይሆን ለባለ ቤቱ ለህዝብ እንተወውና ለማስታወሻ የሚሆን አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ። ይህ ስርዓት ስልጣን በያዘበት ጊዜ በትግራይ የነበረው የተፈጥሮ ልማትና የአረንጓዴ አካባቢ ሽፋን በምን ሁኔታ ላይ አለ? ምን ያክል ፐርሰንትስ ደርሷል? በተለይ ደግሞ ትግራይ የ17 ዓመት ደማዊ ጦርነት ጀምሮ እስካሁን ብዙ ወታደሮች የውጊያ መሳሪያዎችና ተሽከርካሪዎች ያልተለያት አፈር ድቤ እየበላች ያለች ክልል አይደለችም ወይ?

   እስኪ ከምዕራብ ትግራይ ሑመራ ጫፍ ጀምሮ እስከ ምስራቃዊ ትግራይ በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ያለውን ሰራዊትና በተፈጥሮኣዊ ልማት የሚያደርሰውን የደን ጭፍጨፋ እና ውድመት በየትኛው አይን ታይቷል ወይስ ተፈትሿል?
   በየጊዜው በቀላልና ከባድ መሳሪያዎች አይደለም ወይ መፈተኛና መለማመጃ እየሆነች አካባቢ እየተቃጠለ ያለው፥ አረንጓዴ አካባቢን ከማውደም ባለፈም ቀለህና ባሩድ እየተቋቋመ ያለው ተፈጥሮኣዊ አፈር ለቀጣይ አደጋ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው።
   እነዚህና ሌሎች ባዶ የሚያስቀሩ ተግባሮች ተቋቁማ እየሄደች ያለችው ትግራይ በአሁኑ ወቅት በውጭ አካላት የአረንጓዴ ልማት ምርጥ ተሸላሚ ለመባል ያስቻላት ሁኔታ በየትኛው መለኪያ ይሆን? ይህ በወደመ አካባቢ በስጋትና ያለሰላም ዋስትና፤ ልማትና እድገት በተነፈገው ህዝብ ላይ ማላገጥ ነው ሊባሉ ይገባል።

No comments:

Post a Comment