Tuesday, October 17, 2017

ለማንነቱ መስዋእት የከፈለ ህዝብ በጥቂት ከሐዲዎች ማንነቱ አደጋ ውስጥ ሊገባ አይችልም።



    ከጥንት ጀምሮ በአገራችን ኢትዮጵያ ረጅም እውቅና ያለው በአገራችን ውስጥ ሃይማኖታዊ ምርኩዝ ያለው ታሪካዊ አመጣጡ ደግሞ ከቀስተ ደመና የመጣ የሚል የታሪክ አባባል ያስቀመጠ ሰንደቅ አላማችን የአገራዊ ማንነታችን መግለጫ ነው። ስለዚህ ይህ ማንነት ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የሚወክል እንጅ ለወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት የሚወክል መከናነቢያ አይደለም። ባንዴራችን የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ እንጂ የአንድ ስርዓት መግለጫ አይደለም።
    በመሰረቱ በአንድ ሃገር ህዝብ ሲባል የየራሱ ልዩነት ሊኖረው ግድ ነው። ምክንያቱም አንድ አካባቢ የራሱ ልምድና ባህል አለው። የራሱ ማህበራዊ አኗኗር አለው። የራሱ አመጣጥ አለው። በሌላ በኩል ደግሞ የራሱ መሰረታዊ አቀማመጥ አለው። በአገራችን ከባድ መስዋእት የተከፈለውም ለዚህ ነው።
   የአገራችን ታላላቅ አርበኞቻችን ስለሃገራቸው፤ስለህዝባቸው መስዋዕት ከፍለው፤ተሰንክለው ስለሃገራዊ ማንነታቸው ከባድ ዋጋ ከፍለዋል። የአገራችን ሰንደቅ አላማ ለዘላለም ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ይህ ስርዓት ይህንን ከባድ ዋጋ የረሳው ይመስላል።
    በምናስታውስበት ጊዜ በአገራችን ስለሃገራዊ ክብር ብዙ ጊዜ ጦርነቶች ተደርገዋል። በዚህ በተካሄደው ውጊያ ማለቂያ የሌለው ተቆጥሮ የማያልቅ መስዋዕት ተከፍሎ በላይ የምትውለበለበው ባንዴራ አንድ ናት። ምክንያቱም አንዲት አገር አንድ ባንዴራ ብቻ ስለሚኖራት ። አንድ ባንዴራ ደግሞ በአንድ አገር ለሚገኙ ህዝቦች ማንነታቸውን ትገልፅላቸዋለች እንጂ መለመኛና መሸቀጫ አይደለችም። በህዝቦች ምንም እንኳ ብዙ የፖለቲካ ልዩነት ቢፈጠር የማንነት ክብር ግን አይገፈፍም። 
    የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት በውስጡ የህዝብን ጥያቄ ሳይመልስ በአገር ማእከል ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በእኩልነትና በአንድነት ለማኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ሰንደቅ አላማ እያውለበለብሁ ነው ብሎ እየተናገረለት ያለው የማይረባ ተግባር ለራሱ እንደፖለቲካ ብሎም እንደስርዓት በውስጡ ያልተፈታ እንቅፋት እንዳለው የሚያስረዳ ነው።
    አገራዊ ማንነት በማታለል የሚገለፅና የሚንፀባረቅ ሳይሆን በቀናነት ማን እንዴት ይገለፃል። የት ምን ተሰራ የተከናወነ ስኬታማ አገራዊ ፍፃሜ የሚያኮራ ጀግንነት እንደሰው ሰብዓዊ ክብር ያጎናፀፈ የተስተካከለ አስተሳሰብ የተመረኮዘ ፍፁማዊ ሐቅ የተላበሰ ታሪካዊ ሁነት እንጂ ስለግላዊ ጥቅም ተብሎ የሚደረግ ፖለቲካዊ ማንከባለል አይደለም።
    በህገ መንግስቱ በመሰረቱ ሰፍሮ ያለው አርማ አትኩሮት የሚያደርግለት የተማረ ሰው የለም ወይ የሚያሰኝ ሃሳብ አለው። ምክንያቱም የስርዓቱ አርማ  የወያኔያውያንን ፖለቲካ ነው የሚገልፅ እንጂ የኢትዮጵያን ህዝቦች አይገልፅም። ለምን ቢባል የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ማለት አይደለምና።

    የሆነው ሆኖ የአገራችንን ብሔር ብሄረሰቦችን ተስፋ እያጨለመ እንዲሁም ወጣቱን ትውልድ እያሞኘ ስለማንነታቸው መስዋእት የከፈሉ ጀግኖች ሰማዕቶች በየተራራው ዓፅመ ስጋቸውን ረግጦ ስልጣን በእጁ በጨበጡ ጊዜ አራጊ ፈጣሪ ሆነው ህይወት በመክፈል የተገኘውን ክቡር ዋጋ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንነት እያፈነ ዛሬ ይህንን በዓል ለምን ብሎ ነው የሚያከብረው የሚል ብዙ ኢትዮጵያውያንን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኖ ነው የቆየው። የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ግን ባለማፈር ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ድል ተነስተናል። በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ በጭፈራና በዳንኬራ እያከበረው ይገኛል።

    ባለፈው አመት አሁንም እየቀጠለ ያለው ብዙ የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች የማንነት ጥያቄ አንስተው ወያኔ ኢህአዴግ ያልመለሰው የማንነት ጥያቄ የለም የሚል ድፍን መልስ ተሰጥተው ያለፍላጎታቸው ተረግጠው እየተዳደሩ ባሉበት ወቅት ይህንን መልስ አንቀበልም ብለው ስርዕቱን በተቃውሞ ያናወጡ እንደቅማንት የመሳሰሉ ማህበረሰቦችን ደግሞ ወደ ሪፈረንደም እንዲገቡ በማድረግ የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት እንደአመሉ ልክ እንደአለፉት አገራዊ ምርጫዎች ያደርገው የነበረ ተንኮል አሁንም የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመ ትክክለኛ የህዝብ ድምፅ ያልተንፀባረቀበት ውጤት አሰምቶናል።

     የቅማንት ማህበረሰብ ከአማራ ተነጥለን ራሳችን በራሳችን መተዳደር አለብን ብለው ሰፊ ተቃውሞዎችን እያደረጉ በአይናችን እያየን በጀሮኣችን እየሰማን ቆይተን ዛሬ ደግሞ ከስምንት ቀበሌዎች ሰባቱ ቀበሌዎች እንደነበርንበት በአማራ ክልል ውስጥ ተጠርንፈን መቀጠል አለብን የሚል ድምፅ ሰጥተዋል የሚል ውሳኔ አሰምቷል። ሐቀኛነቱን ብዙ ሳንጣደፍ በሂደት ይገለፅልናል።  

    በብሄር ብሔረሰቦች መካከል እያጋጠመ ያለው ግጭትና ወያኔ ኢህአዴግ ደግሞ ራሱ እሳት እየለኮሰ ራሱ እሳት አጥፊና አስታራቂ መስሎ ላይና ታች ሲል ማየት አዲስ ዜና አይደለም። በዚህ ምክንያት ደግሞ በኦሮሞና በኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች መካከል ያጋጠመው ግጭት ብዙ ወገኖች ለሞትና ቁስለት እየተጋለጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ባድማቸውን ትተው ተፈናቅለው ብዙ ስቃይ ደርሶባቸዋል።

    ስለዚህ ባንዴራ ሲባል መሰረቱ በነፃ ሃገር፤ የዜጎች መብትና ዴሞክራሲ በተከበረበት፤ የብሔሮች አንድነት በተረጋገጠበት፤ የህዝብን ማንነት ለመግለፅ እንጂ የአንድ ፓርቲ ፖለቲካዊ ነፀብራቅ መገለጫ አይደለም።
   

No comments:

Post a Comment