Saturday, October 28, 2017

ዝሆኖች ሲጣሉ፥የሚጎዳው ሣሩ



   ሰሞኑን በአንዳንድ ነባር የወያኔ ኢህአዴግ አመራሮችና ካድሬዎች የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ጋር ተያይዞ፣ ቀደም ብሎም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሮቶኮል ኃላፊ ወደ አሜሪካ በሄደበት ጥገኝነት ጠይቆ መቅረቱ በኢትዮጵያ አንጃቦ ያለው አደጋ ፍጥነቱ እየጨመረ መሔዱን ያሳያል።  
   እንደዚህ አይነቱ ክስተት ለመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም እንኳ፣ በአንድ በኩል ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ  የሚያነሱትን ጥያቄና የአፈፃፀሙን ሂደት ሲታይ በቡድኑ የስልጣን እድሜ ውስጣዊ ቡግንጁ አብጦ ራሱ ለፈጠራቸው ውጫዊ ቁስሎች ህዝብንና አገርን አክማለሁ ብሎ ቃል ኪዳንና ፀፀት እየገባ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለ26 ዓመታት ያበጡ ቁስሎች መድኃኒታቸውን ለማግኘት እየተካሄደ ባለው ሁለንተናዊ ትግልና መነሳሳት ጠርዝ ላይ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው።  
   እነዚህ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ስልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ለዚህ አሁን ተፈጥሮ ላለው አደጋ እጃቸውን በማስገባት የራሳቸውን አበርክቶ ሲጫወቱና ሲያደፈርሱ የቆዩ አካላት መሆናቸው ደግሞ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። 
   ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ያስገደዳቸው ምክንያት ምንድን ነው? ባለፉት ጊዜያት ጥያቄያቸውን ለምን አላነሱም? አሁን በአገሪቱ ላይ መፍትሔ አጥቶ ዛሬ ነገ ይፈነዳል እየተባለ ባለበት ወቅት ራሳቸውን ለማውረድ እንዴት መረጡ? ተፈጥሮ ካለው አደጋስ ከተጠያቂነት ማምለጥስ ይቻላል ወይ? ይህ ጥያቄ ሁሉም ለውጥ ፈላጊ ወቅታዊ መልስና መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል እንበልና፣ እነዚህ አካላት ያነሱትን ጥያቄ ተከትሎ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ከሚለጠፉና ከሚያጋልጡ ሃሳቦች መካከል ከብዙዎቹ አንዱን በምሳሌነት አንስተን እንግለፅ።
   በእነዚህ የመንግስት አካላት ተመርኩዘው ከተሰጡ ቁጥራቸው የማይናቁ ሃሳቦች ከስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ የወሰዱት እርምጃ ትክክለኛ፤ ወቅታዊና ህዝባዊነትን የሚያረጋግጥ ውሳኔ ነው የሚል ነው። አዲስ ነገር ባይባልም በዚህም አለ በዚህ እነዚህ አካላት ችግር ሲፈጥሩና ችግሩ ሲፈጠርም እያዩ እንዳላዩ የህዝብ ስቃይና መከራ ምናቸውም ያልሆነ፣ የግል ኑሯቸውና ስልጣናቸው ግን የሚያሳምማቸው ዓበይት የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው። 
   አሁን በአደጋ በተከበቡበት ጊዜ ለግል የሚደረግ ወለም ዘለም ደግሞ ፍፁም ህዝባዊነትን አያረጋግጥም። ህዝባዊነት ማለትማ መጀመሪያ ምለውና ተገዝተው የገቡትን የህዝብ ወንበር በቀናነት፤ በእምነትና በተነሳሽነት ማገልገል ከዚህ ባለፈም ተጠያቂነትን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን አክብሮ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመጠበቅ ወይም ሳይጥሱ ወገናዊነት የሚረጋገጥበት ምቹ ሁኔታ ማመቻቸት ወይም ታጥቆ መታገል ነው።   
   ካልሆነ ግን ህዝባዊ ሃላፊነትን ረስተው ግላዊ ጥቅማቸውን ለማደላደል ወደ ብልሹነት አዘቅትና የረከሰ ተግባር ሲዘምቱ ቆይተው አሁን አደጋ በተደቀነበት ወቅት ከስልጣን መውረድ አለብኝ ማለት ከተጠያቂነት አያድንም። አበው ሲተርቱ ሁለት ዝሆኖች ሲጣሉ፣ የሚጎዳው ሳሩ ይላሉ።  
   ይህ ማለት ደግሞ እነዚህ አካላት በዚህ አደጋ ወቅትና ተያይዞ የመውደቅ ወቅት ለ26 ዓመታት ሙሉ ሲከተሉትና ሲተገብሩት የመጡትንና ያሉትን የቡድኑ አውዳሚ ተግባሮች ዛሬ ህዝብንና ሃገርን ሊያወድም የሚችል የጥፋት ደመና ተከቦ ባለበት እርስ በርሳቸው እየተበላልሉ ከአደጋ ሊያወጣ የሚችል መፍትሔ መተግበር አቅቶት በንትርክና በስልጣን ሽኩቻ ተጠምዶ እንዳለ በግልፅ የሚያሳይ ነው።  
   የእነዚህ በህዝብና በሃገር ሃብት ተንደላቀው በደንባራ ስስትና የስልጣን ጥም እየተጣሉ ችግር ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ውጤትም አሁን እየታየ ያለው መፍረክረክ ነው።   
   ከዚህ ባለፈ አሁን መፍትሔ አጥቶ በየቀኑ በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮኣዊ አደጋዎች እየተጠቃ ያለው ምስኪን ህዝብ እየደረሰበት ያለው ውድመት ለመገመቱ አያስቸግርም። ስለዚህ የወያኔ ኢህአዴግ ውስጣዊ ንትርክና ግጭት ህዝብንና ሃገርን ይዞ እንዳይወድም ሁላችንም ሰላምና ዴሞክራሲ ፈላጊ የሆነ ኢትዮጵያውያን ድላችንን አብረን ልናቀላጥፍ ይገባል።

No comments:

Post a Comment