Wednesday, May 2, 2018

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ውስጥ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጠንክሮ እየቀጠለ መሆኑን ታወቀ፡፡



  ሚያዝያ 23 ቀን 2010 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ፊንጫ ከተማ፣ ሚድሮክ ኢትዮጵያ የወርቅ ቁፋሮ የሚያካሂድበት የስራ ፈቃድ መታደሱ ያስቆጣቸው ነዋሪዎች ቁጣቸውን በአደባባይ ሲገልጹ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይኸው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ውሎ፣ በምስራቅ እና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች ውስጥ ታላቅ ህዝባዊ እንቅስቃሴ መደረጉን መረጃዎች ገልጸዋል፡፡
  ሚድሮክ ኢትዮጵያ በአካባቢው የሚገኘውን የወርቅ ማዕድን ለማውጣት የሚጠቀማቸው ንጥረ ነገሮች፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የጤና ችግር እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡ በከተማዋ ለተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ዋነኛ መንስኤ የሆነውም፣ በኩባንያው አማካይነት እየደረሰ ያለው የጤና ችግር ነው፡፡ ሰኞ ተጀምሮ በጠነከረ ሁኔታ የቀጠለው የኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞኖች ህዝባዊ ቁጣ፤ በአንድ ቀን ልዩነት አድማሱን በማስፋት ማክሰኞ በምስራቅ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ሻኪሶ እና ፊንጫ ከተሞች ውስጥ የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ አውራ የመኪና መንገዶች በእንጨት እና በድንጋይ ተዘጋግተው መዋላቸውን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ እንደዚሁም የንግድ መደብሮች እና የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ መዋሉንም ለመረዳት ተችሏል፡፡
   የሼህ ሁሴን አሊ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ ክልል ከሚያከናውናቸው የማዕድን ቁፋሮ ስራዎች መካከል በጉጂ ዞን ሻኪሶ አቅራቢያ የሚገኘው የለገደንቢ የወርቅ ቁፋሮ አንዱ ሲሆን፤ ከዚህ የወርቅ ምርትም ኩባንያው ግዙፍ ዓመታዊ ገቢ ይሰበስባል፡፡ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ይህን ስራ ለማከናወን የሚጠቀመው የኬሚካል ንጥረተ ነገር፣ እና ወርቁ ተጣርቶ ከወጣ በኋላ በቆሻሻ መልክ የሚደፋው ተረፈ ምርት፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ማስከተል ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ 
 

No comments:

Post a Comment