Sunday, July 28, 2013

በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በአሁኑ ጊዜ የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ አርሶአደሮች ተገደው የውሰዱትን ማዳበሪያ መንግስት እንዲረከባቸው መጠየቃቸውን ከቦታው የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።



በደረሰን ዘገባ መሰረት በዞኑ የሚገኙ በእርሻ ስራ የተሰማሩ ባለሃብቶችና አርሶ አደሮች በአሁኑ ጊዜ በአከባቢው በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት የእርሻ ስራቸውን ማከናወን ስላልቻሉ መንግስት ጫና በማድረግ በውድ ዋጋ እንዲገዙ ያስገደዳቸውን ማዳበሪያ በጥቅም ላይ ስላልዋለና ለኪሳራም ስለተዳረጉ መንግስት መልሶ እዲረከባቸው ያቀረቡትን ጥያቄ በአከባቢው አስተዳደር ተቀባይነት ባለማግኘቱ ማዳበሪያ የጫኑ ተሽከርካሪዎቻቸውን በማቆም በመከራከር ላይ መሆናችውን ለማወቅ ተችላል።
ይህ በእንዲህ እያለ ከተለያዩ የሃገሪቱ አከባቢዎች ስራ ፍለጋ ወደ ሁመራ የሄዱ በሽዎች የሚቆጠሩ የቀን ሰራተኞች በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት የተለመደው የእርሻ ስራ በመተጓጎሉና ስራ ማግኘት ስላልቻሉ ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበት ገንዘብ አጥተው በችግር ላይ እንደሚገኙ ቷውቋል።
በሌላ በኩል በሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ በሸራሮ ከተማ በንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ምክንያት ለአንድ ጀሪካን ውሃ በ 3 ብር ሂሳብ እየተሸጠ ሲሆን ለመግዛት አቅሙ የሌላቸው የከተማዋ ኗሪዎች ጥራቱን ያልጠበቀ የጉድጓድ ውሃ ለመጠቀም በመገደዳቸው ለተለያዩ የውሃ ወለድ በሽታዎች እየተጋለጡ ነው ።
በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ የሞገኙ እንደ ሆቴል የመሳሰሉ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በውሃ እጥረት ምክንያት ስራ ማቆማቸውን ቷውቋል።