Sunday, September 22, 2013

በመላ አገሪቱ በሚታየው የኑሮ ውድነት ምክንያት በተለያዩ ከተሞች የሚኖር ህዝብ ህይወቱን መምራት በማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል።



የኑሮ ውድነት በመላ አገሪቱ እየተባባሰ መጥቷል ፥ በተለይም በአዲስ አበባ ፤ ድሬዳዋና መቐለ አከባቢ የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ከ 2000 ብር በላይ የደረሰ ሲሆን የሌሎች የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋም በከፍተኛ ደረጃ ከጊዘ ወደ ጊዜ ሲጨምር ይታያል ። በዚህም የተነሳ በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የሚኖር ህዝብ በኑሮ ውድነት ምክንያት ህይወቱን በአግባቡ መምራት በማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሁሉም ትላልቅ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የቤት አቅርቦት ችግር ስላለ በቀላሉ የሚከራይ ቤት ማግኘት የሚቻል አይደለም ። ለደላላ ገንዘብ ተከፍሎ የሚገኘውንም ቢሆን ከከተማዋ ዳር ሆኖ አንድ እጅግ ጠባብ ቤት ለመከራየት እስከ 600 ብር በላይ ኪራይ ይጠይቃል።
ቤት አከራዮች ከሚያገኙት ገቢ 40% ለመንግስት ገቢ ለማድረግ ስለሚገደዱ በመንግስት ለሚጠየቁት ግብር ለመሸፈን ሲሉ የኪራይ ዋጋ በተደጋጋሚ ሲጨምሩ ይታያል። ሁኔታው በተከራዮች በተለይም በመንግስት ሰራተኞች ላይ ወርሃዊ ከሚያገኙት ገቢ በላይ እየሆነ ስለሚመጣ በኑራቸው ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ይገኛል።
በአሁኑ ጊዜ የኢህአዴግ ስርዓት በፈጠረው በርካታ ፖለቲካዊ ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ሃገራቸውን እየጣሉ ለመሰደድ በሚያደርጉት ሙከራ ህይወታቸውን የሚያጡ በጣብ ብዙ ናቸው።