Wednesday, November 27, 2013

አንድነታችንና እኩልነታችን በኢህአዴግ መቃብር ላይ ይረጋገጣል!


በህዝብ የተተፋው የኢህኣዴግ ስርአት ። የተለያየ ምክንያቶችን እየፈጠረ ህዝብን በማደናገር የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ሲል እንደ አንድ አላማ ይዞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፣ ይህንንም አላማው ከግቡ ለማድረስ እየተጠቀመባቸው ካሉ ዘዴዎች መካከል። በተለያዩ ስሞች የተሰየሙ በዓላትን  በአዋጅ መልክ እያወጣ ። ህዝቡን የቤቱን ጉዳይ ትቶ በነዚህ በዓላት እንዲያተኩር ማድረግ ነው፣



በዚህም በእያንዳዱ ወር በዓላት ተሰይመው እንዲቀመጡ ተደርጓል፣ እነዚህ በአዋጅ የተቀመጡ በዓላት ። ስርአቱ ለስልጣኑ አስጊ የሆነ ነገር ሲፈጠር የህዝቡን የአተኩሮ አቅጣጫን ለመቀየር አስቦ ከሚያቅዳቸው ሲሆን እንደ አብነት ለመጥቀስ ያክል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በስርአቱ ተግባሮች ተማሮ ስርአቱን በመቃወም እንዳይነሳሳና በመስጋት ለሰራዊቱ ተቆርቋሪ በመምሰል የካቲት 7 የሃገር መከላከያ ሰራዊት በዓል ቀን ሲል ሰየመ።
      ስርአቱ በአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች መሃል እየገባ እየፈጠረው ያለው የመበታተን እርምጃ። ህዝቡ ሊነቃበት በጀመረበት ግዜም ቢሆን። በማሃከላቸው ገብቶ ፍቅር፤ አንድነትና መቻቻልን እንዲሰፍን እንደሚፈልግ መስሎ በመቅረብ ህዳር 29 ቀን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ብሎ በመሰየም በየአመቱ እንዲከበር በማድረግ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ በማሰብ ብቻ በሃገርና በህዝብ ሃብት ይጫወታል፣
      በሌላ በኩል የአገራችን ከተሞች በመብራትና ንፁህ የመጠጥ ውሃ፤  የኑሮ ውድነትና ሌሎች መሰረተ ልማት  እጥረት ባጋጠማቸው ግዜ። የከተማው ነዋሪ ህዝብ ከማንም ግዜ በላይ ተማሮ የስርአቱን እውነተኛ ገፅታና ምስል ሊረዳ በጀመረበት ግዜም። ህዳር 11 የከተሞች ቀን ብሎ በመሰየም። በብዙ ሚልዮን የሚገመት ገንዘብ እንዲወጣ በማድረግ። ዛሬም እንደተለመደው በባህርዳር ከተማ በዓሉን ለማክበር ሽሩጉድ ሲል ይታያል፣
      ለመሆኑ በየትኞቹ ከተሞች ነው በዓላቱ እየተከበሩ ያሉት? እነዚህ ብንፁህ ውሃ እጥረት እየተሰቃዩና ለተለያዩ የውሃ ወለድ በሽታዎች ነዋሪዎቻቸውን በማጋለጥ ለሞት እየዳረጉ ያሉ ከተሞች? እነዛ በመብራት ሃይል እጥረት የምግብ ማብሰያ አጥተው በጨለማ ቤታቸው ሆነው በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ በሚኖሩባቸው ከተሞች? ወይስ በመልካም አስተዳደር እጦትና በተወሰኑ ፈላጭ ቆራጭ ባለስልጣናት አበሳውን እያየ ያለው የከተማው ነዋሪ? በየትኞቹ የማይታወቁ የኢትዮጵያ ከተሞች ነው ይህንን የማታለያ በዓልና ዳንኬራ እየተደረገ የሰነበተው፣
      ከኢህአዴግ የተማርናቸው ተግባራት ካሉ በእያንዳንዱ ወራት የተለያዩ በዓላት በማስቀመጥ ህዝባችንን ከስራ ውጭ ማድረግና በተለይም ለአያሌ ዓመታት ተምሮ ስራ አጥቶ እየተንከራተተ የሚውል የተማረ ወጣት ሃይል በስርአቱ ላይ ተቃውሞ እንዳያስነሳ በዓሎች በመጡበት ቁጥር ተደናግሮ እየጨፈረ እንዲውል ለማድረግ ሆን ተብሎ እየተካሄደ ያለ ነው፣
     አሁንም ለመጪው ህዳር 29 ቀን የሚከበረው የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ቀን የሶማሌ ክልል እንድያዘጋጅ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፣ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለምን ይሆን የተመረጠው? ተረኛ ስለሆነ ወይስ በዓሉን ለማዘጋጀት የሃላፊነት እጣ ስለደረሰው? እዚህ ላይ ልንረዳው የሚገባን ነጥብ አለ።
     የኢህአዴግ ስርአት ሁሉንም የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥቅሙን ማእከል ያደረገ ስለሆነ። በያዝነው ዓመት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንዲደረግ መወሰኑ ዋነኛው ምክንያት። የኦጋዴን ህዝብ የስርአቱን ፀረ ህዝብ ተግባሮች ከመጠን በላይ ስላንገፈገፈውና ከዚህም በመነሳትም የተለያዩ አመፆችና ትግል በማድረግ ላይ በመሆኑ። በክልሉ ሰላም እንዳለና የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን እንደሆነ ለማስመሰል፤ በሚከበረው በዓል አሳብቦ የህዝቡን ቀልብ ለመሳብና እኩልነታቸው እንደተረጋገጠላቸው አስመስሎ። ለአገራችን ህዝብና ለአለም ማህበረሰብ ለማደናገር ያለመ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ የስርአቱ ተንኮል ነው።
      ለማጠቃለል የኢህአዴግ ፈላጭ ቆራጭ ስርአት አገርንና ህዝብን ወደ ውድቀትና ኃላ ቀርነት ለማስገባት የተዘጋጀ ስርአት ስለሆነ። የአገር መከላከያ፤ የከተሞች፤ የብሄር ብሄረሰቦችና የባንዴራ ቀን ወ.ዘ.ተ እያለ በዓላት ቢደረድርም። ለህዝብና ለሃገር አስቦ ሳይሆን የጥቂት ግለሰቦች ጥቅም ለማረጋገጥና ስልጣኑን ላማራዘም አልሞ መሆኑን የሚታወቅ ነው፣
      ስለዚህ ዛሬም ይሁን ነገ የኢህአዴግ ስርአት። በዓላት ለመፈብርክ ስለማይቸግረው ህዝባችን በስርአቱ እኩይ ተግባሮች ሳይደናገር። አንድነቱን ለማጠናከርና እኩልነቱን ለማረጋገጥ፤ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በፍቅርና በአንድነት ተቃቅፎው እንዲኖሩ፤ኢትዮጵያዊነታችን እንዲከበር፤ በማንነታችን እንድንኮራና ችግራችን እንዲያበቃ ከተፈለገ። የስርኣቱ ግብኣተ መሬትን ማቀላጠፍ ይገባናል፣