Sunday, May 11, 2014

በትግራይ ምእራባዊ ዞን ወልቃይት ወረዳ ውስጥ ሚያዝያ 17 2006 ዓ/ም የስርአቱ ካድሬዎች መሬትን ለመሸንሸን በተሰማሩበት ግዜ በህዝቡና በሸንሻኞቹ መሃከል ከባድ ግጭት በመፈጠሩ ምክንያት የሰው ህይወት መጥፋቱ ተገለፀ።



በመረጃው መሰረት በወልቃይት ወረዳ ማይጋባ ቀበሌ ልዩ ስሙ ማይ ሁመር በተባለው አካባቢ በካድሬዎቹ የታቀደው የመሬት ሽንሸና በህዝቡ ተቀባይነት ስላጣ በህዝቡና በስርአቱ ካድሬዎች ከባድ የተኩስ ልውውጥ እንደተካሄደና በወቅቱም 4 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች 3 ሰዎች በከባድ ቆስለው በሽሬና በሁመራ ሆስፒታሎች ገብተው እየታከሙ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አስታውቋል።
     በተከሰተው ከባድ ግጭት ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ  ወገኖች፣-
-    አቶ ነጋ አስፋው የቀበሌው መሬት አጥኚና ሸንሻኝ
-    አቶ እንዳልካቸው ከበደ የቀበሌ መሬት ሃላፊ
-    አቶ ተፈራ መኮነን የቀበሌው የመሬት ጥናት ሃላፊና
-    አቶ ፋሲል ምህረቴ መሬት ሸንሻኝ ሲሆኑ

በከባድ ቆስለው ህክምና ውስጥ ከሚገኙት ደግሞ
-    አቶ ምህረቴ አለባቸው
-    አቶ ካህሳይ መኳንንት
-    አቶ ኢስጠር አንዳርጋቸው መሆናቸውና እነዚህ የሞቱትንና የቆሰሉት ገዳያቸው ማን መሆኑን እስካሁን እንዳልታወቀ ለማወቅ ተችሏል።

    ይህ በንዲህ እንዳለ ለተከሰተው ሁኔታ እንዲያረጋጋ ተብሎ አፍተራሽ ወሉ የተባለውን የእስርቤት ሃላፊ የአካባቢው ተወላጅ ስለሆነ ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ ወደ ቦታው እንደተላከና የአካባቢው ህዝብ ሰብሰቦ መናገር ሲጀምርም እንደዚሁ አይነት የአስተዳደር መንገድ ካላቋረጣችሁ ለመሬታችን ስንል መዋጋትን እንቀጥልበታለን የሚል መልስ እንደሰጡትና በዚህም ምክንያት የታሰበውን የመሬት ሽንሸና ፕሮግራም ለግዜው መቆም እንዳለበት ትእዛዝ ማስተላለፉ መረጃው አክሎ አስረድቷል።