Thursday, May 15, 2014

በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሽራሮ ‘ከተማ የሚገኙ ነጋዴዎች ከአቅማቸው በላይ ግብር እንዲከፍሉ እየተገደዱ በመሆናቸው የተነሳ ህይወታቸውን ለማጥፋት ሙከራ እያካሄዱ መሆናቸው ተገለፀ።



በመረጃው መሰረት የሽራሮ ከተማ ነጋዴዎች ከሚያገኙት ገቢ ጋር የማይመጣጠን ግብር እንዲከፍሉ በስርዓቱ ተላላኪ ካድሬዎች እየተገደዱ ስለሚገኙ በዚህ ሃላፊነት በጎደለው የግብር ክፍያ የተደናገጡት ዜጎቻችን ደግሞ ህይወታቸውን በገዛ እጃቸው የማጥፋት ሙከራ እያካሄዱ መሆናቸው ታወቀ።
   ከአቅማቸው በላይ ግብር እንዲከፍሉ ከተገደዱት ወገኖቻችን አንዱ አቶ ብርሃነ ሓድጉ ሲሆን 50 ሽህ ብር እንዲከፍል በተጠየቀበት ግዜ የተጠየቀውን ገንዘብ ለመክፈል አቅም ስለሌለው መፍትሄ ለማግኘት ወደ ሚመለከተው አካል በመሄድ ቅሬታውን በሚያሰማበት ሰዓት የሚመለከታቸው አካላት የተወሰነብህ ገንዘብ ትክክል ነው ብለው ምላሽ በሰጡት ወቅት በዚህ ተግባር የተናደደው ይኸው ዜጋ ታጥቆት በነበረው ሽጉጥ ህይወቱን ለማጥፋት ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ህይወቱ ሊተርፍ እንደቻለ ያገኘነው መረጃ ጨምሮ አስታወቀ።
    በተመሳሳይ የሽራሮ ከተማ ነጋዴዎች ከረጅም ግዜ ጀምረው ከአቅማቸው በላይ ግብር እንዲከፍሉ እየተገደዱ እንደመጡ የገለፀው ይህ መረጃ ከነዚህም መካከል አቶ አለነ አባይ የተባለ የሰሊጥ ነጋዴ 50 ሽህ ብር፤አቶ ግርማይ ገብረሂወት(ወዲ ጉራ) በሚል ቅጥያ ስም የሚታወቅ የሸቀጣ ሸቀጥ ድርጅት ባለቤት 50 ሺህ ብር፤ አቶ በርሀ ሱዑዲ የቢራ ማከፋፈያ ድርጅት ባለቤት 500 መቶ  ሽህ ብር እንዲከፍሉ የተጠየቁ ሲሆን ሌሎች ነጋዴዎችም የሚገኙባቸው ሲሆኑ በዚህ የተነሳ የሽራሮ ከተማ ነጋዴዎች  ለክሳራና ለድህነት እየተጋለጡ መሆናቸው ታውቋል።