Tuesday, May 13, 2014

በትግራይ ክልል የሚገኙ የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ባለስልጣናት በህዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እየቀነሰ ስለመጣ ነባር የህ.ወ.ሃ.ት ታጋዮችን በገንዘብ በማታለል ደጋፊያቸው እንዲሆኑ ያደረጉት ሙከራ እንደተነቃባቸው ታወቀ።



የወያኔ ኢህ.አዴ.ግ  ስርዓት መሪዎች ለመጭው 2007 ዓ/ም ሊያካሂዱት ያሰቡት ምርጫ በህዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ዝቅተኛ መሆኑን ስለተረዱ ይህንን ለመሸፈን ነባር ታጋዮችን በጥቅም በመደለል ከጎናቸው ለማሰለፍ “ሚያዝያ 14/2006 ዓ/ም የጡረታ መብታችሁ ስለ ተስተካከለላቹህ ወደ ዞናችሁ ሂዱ” የሚል ትዕዛዝ ማውረዳቸው ተገለፀ።
   ይህ ነባር የህወሃት ታጋዮችን  ከጎናቸው ለማሰለፍ ተብሎ ወደ ዞኖች የተላከው ደብዳቤ ይዘትም “እናንተ ጀግኖች ታጋዮች ለህዝብ መብት ብላችሁ አኩሪ ጀግንነት እየፈፀማችሁ ብትቆዩም እንኳን ድርጅቱ ግን በአቅምና ብቃት ማነስ ያለምንም ክፍያ እንደጣላችሁ የሚታወቅ ሆኖ አሁን ግን ሊክሳችሁ ስለተነሳሳ እንድትተባበሩ እንጠይቃለን” የሚል እንደሆነ የደረሰን መረጃ አስታውቋል።
    በአለፈው 17 ዓመታት ታግለው በ1984ና በ1985ዓ/ም ያለምንም ክፍያ የተጣሉ ታጋዮች በበኩላቸው እንደገለፁት “ለ23 ዓመታት የሚያየን አጥተን በድህነትና ህመም ስንሰቃይ መቆየታችንን እያወቃችሁ አሁን ግን እንደልማዳችሁ እኛን ለማታለል የጡረታ መብታችሁ ይጠበቅላችኋል ማለታችሁ የሰው ሃይል ለመያዝና የስልጣናችሁን እድሜ ለማራዘም የፈጠራችሁት መላ ነው ሲሉ እንደመለሱላቸው ታውቋል።