Friday, May 9, 2014

በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ አመፅ ምክንያት በማድረግ ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ!



የህወሃት ኢህአዴግ ስርአት በህዝቡ የተከፈለውን መስዋእትነትና የደረሰው የአካል ጉዳት ተጠቅሞ ስልጣን ላይ ከወጣበት ማግስት ጀምሮ በህዝባችን ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል እየፈፀመ መምጣቱንና አሁንም እየቀጠለበት መሆኑን ሁሉም ያገራችን ዜጋ የሚያውቀው ሃቅ ነው።
     ስለ ሆነም ከህዝቡ ፍላጎት ውጭ በስልጣን ላይ የሚገኘው አምባገነን ስርአት ህዝቡን- በጎሳ፤ ብብሄርና በሃይማኖት ከፋፍሎ ቀጣይ  በግጭትና በትርምስ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ እጁ በማስገባት መብታችን ይከበርልን ብለው ለጠየቁ አያሌ ዜጎቻችን ሂወታቸው እንዳሳጣቸውና በ 10 ሺዎች ለሚገመቱ ወገኖችም እስር ቤት ውስጥ ታጉረው እየተሰቃዩ ናቸው።
    የህወሃት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ፀረ ህዝብ ስርአት እስካሁን ሲከተለውና ሲያራምደው የቆየውን ፍፁም ህዝባዊነት ያልተላበሰው ፋሽስታዊ ባህሪውና ብልሹ አስተዳደሩ በወለደው ኢ-ዴሞክራሲያዊ አሰራሩ ምክንያት ሰላማዊ ጥያቄ ባነሱ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች በሆኑ ተማሪዎች ላይ ዘግናኝና ህዝብን እያሰተዳደርኩ ነኝ ከሚል ስርአት የማይጠበቅ ፀረ ህዝብ እርምጃ በመውሰድ በርከት ያሉ ዜጎቻችን ሂወታቸው እንዲያጡ አድርጓዋል።
     ይህ በህዝቡ ላይ ያጋጠመው እሳዛኝ ፋሽስታዊ ድርጊት። ስልጣን ላይ የሚገኘው ገዢው ስርአት በትእቢት ተወጥሮ ከህዝቡ ጋር ሳይወያይና ሳይተማመን በልማት ስም በሚፈፅማቸው ከህግ ውጭ የሆኑ እኩይ ተግባራት በህዝብ ለሚነሱ የመብት ጥያቄዎች ሁሌ በሃይል እየረገጠ የመጣና በመርገጥ ላይ ያለ ሲሆን በዚህ በሃገራችንና በህዝባችን ላይ በመፈፀም ላይ ባለው እኩይ ተግባሩ ጊዜው ጠብቆ የሚያስጠይቀው ነው።
 
    ስለዚህ በኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ የተፈፀመው ግፍ። የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ በፅኑ እንደሚቃወመውና ብሎም እንደሚታገለው በመግለፅ እየተፈፀመ ያለው ግፍና በደልም የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርአት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ በባሰ መልኩ እንደሚቀጥል በማዝገንዘብ አሁንም ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎሳ፤ ከብሄርና ከሃይማኖት ልዩነት ነፃ ሆኖ ትግሉን በማጠናከር የስርአቱን እድሜ ማሳጠር እንደሚገባው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ  /ትህዴን / ጥሪውን ያቀርባል።            
   

የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ  /ትህዴን /
       ጉንበት 1-2006 ዓ/ም
ድል ለጭቁኖች