Friday, May 9, 2014

ስልጣን ለአንድ ብሄር የበላይነት ለማረጋገጥ ተብሎ የሚበረከት ስጦታ አይደለም!



በትግል ወቅት ይሁን አገር ለሚያስተዳድሩና ስልጣን ላይ ለሚወጡ አመራሮች የመሪነቱ ቦታ የሚሰጣቸው የግል ጥቅማቸው፤ ቤተሰባቸውና ዘመድ አዝማድን ለመጥቀም ተብሎ የሚስጣቸው ገጸ በረከት ሳይሆን በቅድምያ የህዝቡን አደራ ጠብቀው ለማገልገል ተብሎ እንደሆነ ይታወቃል።
     በአለማቸን የሚገኙ ባለ-ስልጣኖች አንድ አይነት አስተሳሰብና በጎ አመለካከት ይኖራቸዋል ብሎ መጠበቅ የሚታሰብ አይደለም። ባገራችን ያለው ስርአት ይሁን በግል ባለ-ስልጣኖች ላይ የነበረው አስተሳሰብ ማለት ራሳቸውም ጭምር የሚገልፁትና የሚያስተምሩበት የፕሮፖጋንዳ መርህ ከትግሉ መጀመሪያ ጀምረው ሲያስተጋቡት የነበረው ትልቁ መፈክር ስልጣንን  ለህዝብ ማስረከብ፤ የስልጣን ክፍፍሉ የአንድ ብሄር የበላይነት የሚያጎላ ሳይሆን የሁሉም ብሄር ብሄረሰባቦች እኩል ተሳታፊነት የሚያረጋግጥ መሆን ይገባዋል የሚሉና ሌሎችም እንደነበሩ ይታወቃል።
     ቢሆንም መፈክሩና ተግባሩን በማገናኘት ላይ አቅሙ የተሳናቸው የያኔው የትግሉ መሪዎችና የአሁኑ ያገራችን የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ሽማምንቶች ግን ግላዊ አመለካከት እንዲኖር ሁኔታ በማይፈቅድበት ወቅትና አካባቢም ቢሆን መነሻው ስልጣንን ያደረገ በርካታ ችግሮች የሚከሰቱበትና ግልፅና ድብቅ በሆነ መንገድ ራስ በራሳቸው የሚጠፋፉበት መድረክ እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል።
    ከስልጣን እንዲወርድ ለተፈለገው ተደራጅቶ ማጥቃትና   የሃሰት ወንጀሎችን መፈበረክ ከተቀመጠበት  ሃላፊነት ማውረድና ሞራሉና ወኔውን በሚነካ ደረጃ በመገምገም ከትግሉ መስመር እንዲነጠል ማድረግ፤ በትግሉ ውስጥ ትልቅ ሚና ለነበራቸው ታጋዮች ማንገላታት ማሰር ማሰቃየትና መግደል ከብዙዎቹ ጥቂቶች የወቅቱ አረሚናዊ ተግባራት እንደነበሩና ባጠቃላይ በህዝባዊ ወያኔ ትግል ውስጥ መነሻው ስልጣንን ያደረገ  በነሱ አጠራር በህንፍሽፍሽ ደረጃ የሚታወቅ በድርጅቱ ውስጥ የመተላለቅ ታሪክ መካሄዱ በተለይ ትግሉን በቅርብ የሚያውቁት ወገኖች ጠንቅቀው ያውቁታል።
     የወያኔ ስርአት ባለ-ስልጣናት የለመዱትን ፀረ ህዝብ አሰራር እንደ ባህሪ ተለማምደውታልና አገር ውስጥ ከገቡና መንግስትነት ከተቆጣጠሩ ማግስት ጀምሮውም የነበረው የስልጣን ክፍፍል ማለት በዲሞብላይዘሽን ስም ቀና መንፈስና ልቦና ይዞው ሂወታቸውን ለትግልና ለመስዋእትነት አስረክቦው ለድል ላበቋቸው ታጋይ በረሃ ላይ ጥለው ከበታተኗቸው በኃላ ወሳኝ የተባለው ስልጣን ለግላቸው ተቆጣጥረው አገሪትዋን ያለ ተቃውሞ እንዲቆጣጠሩዋት በማሰብ ለማስመሰል ብለው ለአንዳንድ አደርባዮች ወደ ስልጣን እንዲወጡ አድርገዋቿል፣ ይህም ቢደረግም ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የተካሄደው ትራጀዲ ሆን ተብሎ ለማስመሰል የተደረገ መሆኑን ስለ-ደረሰበት ሃሳቡ ከመግለፅና ከመቃወም ወደኃላ ያለበት ግዜ የለም።
     ጀነራል ሳሞራ የኑስ  በራሱ ምክንያትስልጣኑ ለመውረድ በተዘጋጀበት ግዜና። እሱን የሚተካ ማን ይሁን በሚል በጠቅላይ ምኒስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ በተመራው ስብሰባ ላይ ሌተናል ኣበባው ታደሰ መሆን ይገባዋል ብሎ ላቀረበው ሃሳብ ፕረዚደንትነት ለኦሮሞ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተርነትና የኢታማዦር ሹም ስልጣንን ለትግራዮች የሚለውን የስርአቱ ይፋዊ አሰራር ለማጠናከር በማሰብ “የለም አይሆንም” ሌተናል ጀረናል ሰአረ መኮነን ወይም ሌተናል ዮውሃንስ ገ/መስቀል ነው ሳሞራን መተካት የሚገባቸው ተብሎ በቀረበው ሃሳብ ላይ በሃይለማርያም ደሳለኝና በነሰኣረ ሞኮነን ደጋፊዎች መሃል ትልቅ መቃቃር እንደተከሰተና የአደባባይ ምስጢር እንደሆነ ሰንበትበት ብሏል።
     የትግራይ ብሄር ተውላጅ ይሁን የኦሮሞ፤ የአማራ ይሁን የአገው፤ የደቡብ ይሁን የጉሙዝ ከየትኛው ብሄር ይፈጠር ማን ለስራው በብቃት ይወጠዋልና ያገራችን ህዝቦች ስልጣን ላይ ያላቸውን እኩል ተሳታፊነት በሚያረጋግጥ መንገድ መሆን አለበት የሚለው ቀና አስተሳሰብ መምጣት ሲገባው የስልጣን ጥም መለያቸው የሆኑ የህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች በእንደዚህ አይነት ኋላ ቀር አስተሳሰብ ተጨማልቀው ማየታችን አዲስ ባይሆንም እየተጠቀሙበት ያለው ዘረኛ አካሄድ ግን አደገኛ መንገድ በመሆኑ ሁሉም ይመለከተኛል የሚል ያገሪቱ ዜጋ በትኩረት ሊከታተለውና ሊታገለው ይገባል።