Friday, June 13, 2014

በሽሬ እንደስላሴ ከተማ የሚኖሩ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ድርጅት ታቅፈው መስራታቸው ለውጥ ሳይሆን ኪሳራ እያጋጠማቸው መሆኑን በስርዓቱ ሃላፊዎች በተደረገላቸው ስብሰባ ላይ መናገራቸው ታወቀ።



በምንጮቻችን መረጃ መሰረት በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሽሬ እንደስላሴ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ድርጅት ታቅፈው ሲሰሩ የቆዩ በርካታ ወጣቶች በዞንና ወረዳ አስተዳዳሪዎች ሰኔ 1 /2006 ዓ/ም በተካሄደው ስብሰባ ላይ  “ጥሩ ገቢ አግኝተን ኑሮአችንን እንደለወጥንና እንደአደግን ተደርጎ የቀረበው ሪፖርት ፍፁም እኛን የሚገልፅ አይደለም” ሲሉ ወጣቶች እንዳጣጣሉት ታውቋል።
   ተሰብሳቢ ወጣቶች በአስተዳዳሪዎች የቀረበውን ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ ባቀረቡት ሃሳብ “የሽሬ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ድርጅት በመታቀፋችን  ዕዳ  ተሸካሚዎችና ለኪሳራ ተጋለጥን እንጅ ያገኘነው ማህበራዊ ለውጥ የለም” ካሉ በኃላ “ እንደ አለፈልን አስመስላችሁ ያቀረባችሁት ሪፖርትም ትክክል አይደለም’’ሲሉ በአንድ ድምፅ እንደኮነኗቸው ለማወቅ ተችሏል።
    በተጨማሪም ወጣቶች“ለእናንተ ሪፖርት እንዲመቻችሁ ከትላልቅ ሃብታሞች ጋር እየሰሩ ተለውጠዋል ትሉናላችሁ እኛ ግን ለአራት አመት ሙሉ የሰራነው ዕጣንና ለሶስት አመታት ያመረትነው ብሎኬትና ሌሎችም የሚገዛን አጥተን ባክኗል እናንተም የገበያ ትስስር ስለሌላችሁ ለኪሳራ እንደተጋለጥን እያወቃችሁ ከብረዋል ተለውጠዋል ማለታችሁ በጣም የሚያሳዝን ጉዳይ ነው”እንዳሏቸው ታውቋል።
   እንደዚህ ዓይነት ጠንካራ ጥያቄ ካነሱት ወጣቶች መካከል ወሉ አርአያ የተባለ በዕጣን የቅርንጫፍ ጸሃፊ ሆኖ ይሰራ የነበረ ሲሆን “ከሌለ ሪፖርት ከምታቀርቡ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ለምን አትሰሩም”ሲል እንደተቃወመ ታውቋል።