Thursday, August 14, 2014

በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሽራሮ ከተማ ሙሴ ቀበሌ የሚገኙ በእርሻ የሚተዳደሩ ወገኖቻችን መኖርያ ቤታቸውን በአካባቢው አስተዳዳሪዎች በሓይል እየተነጠቁ መሆናቸውን ምንጮቻችን ከአካባቢው አስታወቁ።



    እነዚህ ከ20 በላይ የሚሆኑ የሽራሮ ወረዳ  ከተማ ሙሴ ቀበሌ  ማይ አርቃይ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎቻችን በጥርጊያው አካባቢ በህጋዊ መንገድ መሬት ተሰጥቷቸው ቤት ሰርተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩበት ለነበረው ቤታቸው በአሁኑ ወቅት የአካባቢው አስተዳዳሪዎች መኮነን( ቡልቱግ) በሚል ቅጥያ ስም የሚታወቀው) ከፖሊሶች ጋር በመተባበር የድሆችን ቤት በሓይል በመቀማት ለአንድ በሽሬ ከተማ ለሚገኝ የሆቴል ባለቤት እንደሰጡት ‘ለማወቅ ተችሏል።
     እነዚህ ገበሬዎች በቆርቆሮና በድንጋይ ለተሰራው ቤታቸው መተኪያ እንዲሰጣቸው በማለት ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም የስርዓቱ ካድሬዎችና አስተዳድሮች ግን ሰጠናቸዋል ለማለት  ለእያንዳንዳቸው 10ሺህ ብርና የተወሰነ ቆርቆሮ እንደሰጧቸው የገለፀው መረጃው  ለዚህ እኩይ ተግባር ሰለባ የሆኑ አርሶ አደሮች ግን የሁለት ቤት ምድር አርማታ  ከሞሉ በኋላ ገንዘቡ ስለተጨረሰባቸው የጀመሩትን ቤት መሙያ  ዳግመኛ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ለሚመለከታቸው አካላት በጠየቁበት ግዜ ካሁን በኋላ ገንዘብ የሚባል ነገር አንሰጣችሁም ከፈለጋችሁ መሸጥ ትችላላችሁ የሚል መልስ እንደሰጧቸው መረጃው አስታውቋል።
   እነዚህ በስርዓቱ መኖርያ ቤታቸውን በሓይል ተቀምተው ከነቤተሰቦቻቸውና ነፍስ ያላወቁ ህፃናትን ይዘው በርሃ ላይ ተጥለው ፀሃይና ብርድ እየተፈራረቀባቸው  በስቃይ ከሚገኙት ውስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ አቶ በርሁ ተክላይ ግደይ፤ አቶ ፍሰሃ ብርሃነና ሌሎችም ስማቸው ያልተጠቀሱ በርከት ያሉ ወገኖቻችን እንደሚገኙባቸው ምንጮቻችን የላኩልን መረጃ ጨምሮ አስታውቋል።