Sunday, February 1, 2015

የየካቲት 11 የህወሃት ልደት በዕዓልና የትግራይ ህዝብ አስከፊ የንሮ ሁኔታ !!



የህወሃት ኢህአዴግ ባለስልጣኖች መጀመርያውኑ የትጥቅ ትግል ሲጀምሩ  በወቅቱ የነበረው አቋማቸው ፋሽስታዊ የደርግ  ስርዓት ማስወገድ፤ ብልሹ አስተዳደርና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አሰራሮችን ማጥፋት ዋናው አላማቸው እንደሆነ አስበው ቢነሱም ይህንን መፈክር አንግበውና ያን ሁሉ መስዋእት ተከፍሎ የደርግ ስርዓት ከተወገደ በኋላ ግን ጥቂት ወራቶች እንኳ ሳያስቆጥሩ የስለላ መዋቃራቸው በማስፋፋት ያገሪቱ ሃብት በመውረር፤ የግል ጥቅማቸው ወደ ሟሟላት አሳፋሪ ተግባር ተሰማርቷል።  
    ህወሃቶች ረጅም ሳይጓዙ አጠቃላይ አሰራራቸው ቤተሰባዊ ቅርፅ ይዞና ሙሱና በውስጣቸውና በአጃቢዎቻቸው ውስጥ እንደ ህጋዊ አሰራር በመውሰድ እየተጠቀሙበት መሆናቸው ህዝቡ በሚገባ እንደሚያውቀውና የአለም ባንክና አይ,ኤም ኤፍ እንዳረጋገጡትም ከ10 ቢልዮን ዶላር በላይ የሚገመት የህዝብና የሃገር ሃብት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ውጭ አገር እንዲወጣ ማድረጋቸው ተረጋግጠዋል።     
    በመሆኑም ያገራችን ህዝቦች  በስራ አጥነትና በስደት እየተሳቃዩ ባሉበት ባሁኑ ግዜ የህወሃት መሪዎችና አጃቢዎቻቸው ግን የሃገራችን ሃብት እየዛቁ በልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ስም በአውሮፓና በአሜሪካ ባንኮች እያስቀመጡና ለልደታቸው በዓል ማስከብሪያ በማለት በብዙ ሚልዮን የሚገመት ገንዘብ እያባከኑ ይገኛሉ።
   እነዚህ የስርዓቱ ሹማምንቶች ትናንት ለህዝቡ እኩልነትና አንድነት ብለን መስዋእት እየከፈልን ነን ማለታቸውን ረስተው አሁን ላይ ደርሰው ያገሪቱ የድህነት ሁኔታ ግምት በማያስገባ ሁኔታ ራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ለህክምናና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በመሄድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር እያፈሰሱ ሂወታቸው ለማቆየት ማሰባቸው በዘመነ ደርግና አፄዎቹ እንኳን ያልታየ አስነዋሪ ተግባር መሆኑን የሚካድ አይደለም።
    እናም በአሁኑ ሰዓት የህወሃት መሪዎች የየካቲት 11/ 40የልደት በአል  ለማክበር በሚል ስም ያን ያህል ዝግጅት’ና ቡራ ከረዮ ማብዛታቸው ሲበዛ የሚያስነውርና ችግር ላይ ለወደቀው ህዝብ ያላቸው ንቀትና ደንታ ቢስነታቸው የሚያሳይ መሆኑን የሚያጠራጥር አይደለም፣ ይህም ህወሃት ገና ከጅምሩ ድብቅ አላማ እንደነበረውና በውስጡ ከፍተኛ የግለኝነት አመለካከት የተጠናወተው ድርጅት እንደነበር  ቁልጭ እድርጎ የሚያሳየን ሃቅ ነው።
   እነዚህ የዘመ ፀረ ህዝብ መሪዎች ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሚባል፤ ሙሰኞችን እያጋለጠ ህግ ፊት የሚያቀርብ፤ በርካታ የስርዓቱ አገልጋዮችና የህግ ባለ ሙያዎች ያሉበት አንድ ትልቅ ተቋም ገንብተናል ቢሉም ተቋሙ ግን ሙስናን የሚያጠፋ ሳይሆን በባሰ መልክ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር እያደረገ መሆኑን ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቋል።
   አንዳንድ በታችኛው የስልጣን እርከን ሆነው ነገር ግን የስርዓቱ ታማኝ ካድሬዎች በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ከፍተኛ ሃብት ያከማቹ ግለ ሰዎች ከህዝቡ ዓይን መደበቅ የማይችሉ ስለሆኑባቸው የህዝቡን ስነ ልቦና ለመቀልበስና እውነተኛ ያገር ተቆርቛሪ መሪዎች እንደሆኑ ለማስመሰል ህግ ፊት በማቅረብ የሸፍጥ ድራማቸው ሲያሳዩን ይስታዋላሉ ይህን የተንኮል አሰራራቸው ግን ህዝቡን ለማደናገር እንጂ ሙሰኞችን ወደ ፍርድ በማቅረብ በፈፀሙት ወንጀል ተገቢ ቅጣት እንዲሰጣቸው በማሰብ አይደለም።
   ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ወጣት የተማረ ኃይል ባሁኑ ግዜ ተምሮ ስራ የማያገኝበት፤ አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እናሰልፋታለን ተብሎ እየተወራ ባለበት ባሁኑ ግዜ ስደት፤ ረሃብና ድንቁርና በሰፊው በተስፋፋበት፤ አብዛኛው ያገሪቱ ህዝብ ሃብቱ በእኩል የማይጠቀምበት ብቻ ሳይሆን ጥቂት ባለስልጣኖችና ቤተሰቦቻቸው የሚፈነጥዙበትና አብዛኛውን ጭቁኑ ህዝብ የበይ ተመልካች ሁኖ በባዶ ሆዱ እየተሰቃየ ኑሮውን የሚገፋበት ሁኔታ ላይ ይገኛል።
   ስለሆነም ከዚሁ ፀረ ህዝብ መንግስት ተላቅቀን ሰላም፤ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት ሃገር ለመገንባትና የህዝቡን አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የህወሃት የልደት በዓልና አገራችን ውስጥ ያሉትን አመራሮች በመቃወም የእምቢ አልገዛም ድምፃችንን ማሰማት ይገባናል።