Thursday, March 19, 2015

ሰማእታትን እንደ ሽፋን ተጠቅሞ ለምርጫ መዘጋጀት ታሪካዊ ስህተት ነው!!



    የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት። የህዝቡን ፈቃድና ታማኝነት እስካላገኘ ድረስ። የስልጣን እድሜውን ለማስቀጠል ሲል። መጨረሻ የሌላቸው የተጋነኑ የሃሰት ድራማዎች በማሳየት ህዝቡን ለማደናገር መሞከሩ እምብዛም የሚያስገርም አይደለም፣
    የኢህአዴግ ባለስልጣናት። የሰማእታትና የህዝቡን አደራ ወደ ጎን በመገፍተር። የያዙት ስልጣን ተጠቅመው። የግል ሃብታቸውን በማካበት ላይ ተዘፍቀው። በህዝቡ ኑሮ ላይ ቅንጣት ታህል የማህበራዊ ኑሮ እድገት ለውጥ ያላመጡ መሆናቸውን እያወቁ። በምርጫው ዋዜማ ላይ ትልቅ ጉዞ እንደተራመዱና ለወደፊቱም ብዙ መስራት እንደሚችሉ ሆነው ቃል ሲገቡ እየታዘብናቸው ነው፣
    እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለፀጋ የሆነች አገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና መልካም አስተዳደር ባለመኖሩ። ምክንያት ሁሉ ግዜ በድህነት ተርታ ላይ እንድትጠራና። መሪዎቿ በሙስና ውስጥ የትዝፈቁና ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብት በመጣስ ተግባር ላይ የተሰማሩ  በመሆናቸው። በቀጣይ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንድትገኝና። ባጠቃላይ አገራችን ጥቂቶች እንደፈለጉ የሚፈነጥዙባት። አብዛኛዎቹ ደግሞ በድህነት ውስጥ ተዘፍቀው የሚሰቃዩባት አገር እንድትሆን ተፈርዶባታል፣
   ዛሬ! የህወሃት መሪዎች ከ24 ዓመት በፊት የፈጸሙትን ክህደት። አሁንም እንደለመዱት። የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል በሁሉም አቅጣጫዎች ተፋፍሞ ባለበት ባሁኑ ግዜ። ተደናግጠው። አሁን ላይ ደርሰው የጀግኖች ሰማእታትን ስም ተጠቅመው። ምርጫን አስመልክተው ቅስቀሳ ለማድረግ መሞከራቸው። እጅግ የሚያሳፍር ርካሽ ተግባር ነው፣    
    የካቲት ወር። በትግራይ ህዝብ ትግል። ልዩ የጀግንነት ታሪክ ያላትና። ከህዝቡ ህሊና የማይጠፉ ፍጻሜዎች እንዳሏት ሁሉም የሚመሰክረው ሃቅ ነው፣ ነገር ግን በህዝቡ ትግል ተንጠልጥለው ወደ ስልጣን የወጡትን ጥቂት ባለስልጣናት። አንድ ይበቃችኃል ሳትልና የልጆቿን ወግ ማእርግ የመድረስ ምኞት ሳታስቀድም። እልልታ እያሰማች 4ና 5 ልጆችዋን ወደ ትግሉ ያሰለፈች የጆግኖች እናት። በልጆቿ መስዋእትነት የተገኘውን የድል ፍሬ ከመጠቀም ይልቅ። በተገላቢጦሽ ወርቅ ለሰጠ ጠጠር እንደመስጠት ሆኖ። አንቀልባዋን ገልብጣ የወላጅ መሃን እንድትሆን ተደርጋለች፣
    አዛዥ በሆነው የህወሃት አመራሮች አካሄድ። በልጆቻቸው ሞት ምክንያት የሃዘን እንባ እያነቡ የአይናቸውን ብርሃን ያጡ ወላጆች የሉም? መልእክት ያልላከ በሂወት እንደሌለ አስቡት ተብለው መርዶ የተነገራቸው ወላጆች የሉም? እንደ እድል ሆኖ ከትግሉ ወላፈን የቀሩት ታጋዮች። ያለ አንዳች ድጋፍ ጦርነትና ድርቅ ወደ ተፈራረቀባት መሬትና ቤተሰቦቹ አልተባረረም እንዴ? በጦርነቱ ምክንያት አካላቸው የተጎሳቆሉና እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው መስራት የማይችሉት ታጋዮች። ዳንሻ በረሃ ላይ ተጥለው እንዳልቀሩ። የህወሃት መሪዎች አሁን ላይ ደርሰው የአዞ እንባ ማንባታቸው። ፋይዳው  ምን ይሆን? 
   የኢትዮጵያ ህዝብ የተፈጸሙትን በደሎች ያስታውሳቸዋል ብቻ ሳይሆን ሁል ግዜ ከልቡ የማይፋቁ ጥቁር ነጥቦች ናቸው፣ የወያኔ ኢህአዴግ ተግባሮች  የጀግኖቹን መስዋእትነትና አካል መጉደልን ተጠቅመው። የስልጣን እድሜያቸውን ለማራዘም እያካሄዱት ያለው መወራጨት። “የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማዕድ እንዲሉ” የጀግኖችን መስዋእትነት እንደ ሽፋን ተጠቅመው ለምርጫ መቀስቀሻነት ለማድረግ ማሰባቸው። ታሪካዊ ስህተት ከመሆን አልፎ። ከባህሪያቸው ውጭ የሰማእታትና የህዝቡ አክባሪዎች ሊሆኑ አይችሉም፣