Tuesday, May 5, 2015

ለበደልና ለጭቆና የተፈረደ ህዝብ ለኢህአዴግ ምርጫ የሚሆን ግዜ የለውም!!



   በአገራችን ስልጣን ላይ የሚወጡ የገዢዎች ስርዓትና አመራሮች የህዝቡን አደራ በሚክዱበት ግዜ ሰፊውን ህዝብ የተሻለ ለውጥ ስለሚሻ በላዩ ላይ የሚፈፀሙ በደሎች ለማስወገድ ሲል የእምቢ አልገዛም ድምፁን እያሰማና ጨቋኞቹን እያንበረከከ አሁን እስካለበት ደረጃ ደርሷል ብቻ ሳይሆን እስካሁንም ቢሆን በዚህ ሂደት ላይ እየቀጠለበት ይገኛል።
   የኢትዮጵያ ህዝብ በላዩ ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆናና ግፍ ታግሎ ለማስወገድ ሲል ወገቡን አጥብቆ አኩሪ ገድል እየፈጸመ የመጣ፤ በአለም መድረክ ላይ ልዩ ታሪክ ያለው ህዝብ ነው። ሉአላዊነቱንና ክብሩን ለመድፈር በጭፍን አይን የመጡትን ሃይሎች ክንዱን በማስተባበር ወገባቸውን በመስበር ሃፍረትና ውርደት ተሸክመው እንዲሄዱ ያደረገ ጀግና ህዝብ ነውና። በዚህ ዘመን ያለን አዲስ ትውልድም ቢሆን የአባቶቻችን ገድል ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍና ይህን የተቀደሰ ታሪክ ደግመን ለማስመስከር አሁንም ቢሆን ለለውጥና ለእድገት እንድንበቃ ኢህአዴግን ከስልጣኑ ለመፈንገል በፅናት መታገል ይጠበቅብናል።
    በአሁኑ ግዜ በአገራችን ውስጥ ከፋፋይና ብሄር ከብሄር በጎሪጥ እንዲተያዩና እንዲጋጩ ምክንያት እየሆነ ያለው በየግዜው ወደ ስልጣን የሚመጡት መሪዎች በሚያራምዱት ፀረ አንድነት ፖሊሲና ዲሞክራሲያዊ አገር ላለመገንባት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም።
   ህዝባችን ባለፉት የዘውድ አገዛዞች፤ ፋሽስታውያንና ፈላጭ ቆራጭ ያገራችን ስርዓቶች እንደተረገጠና ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንደተጣሰ አውቆ የይገባኛል ጥያቄ ማንሳት ይቅርበትና። ፍፁም እንደማይመለከተው ታይቶ የጥቂት ሹሞኞች አገልጋይ ሆኖ እንዲጨቆን፤ ንቃተ ህሊናውን እንዳያሳድግ በችግር ላይ ችግር ተደራርቦበት አስከፊ ህይወት እንዲመራ የተፈረደበትና አሁንም በኢህአዴግ ስርአት በባሰ መልኩ እየታየ ያለበት ሁኔታ ላይ ይገኛል።
    በላዩ ላይ ግፍና በደል እየተፈጸመበት ራሱን አጎንብሶ መቀበል ታሪኩና ማንነቱ የማይገልፀው ህዝባችን በወቅቱ አምባገነን ስርአቶች ላይ የእምቢ አልምበረከክም ትግሉን በማቀጣጠል፤ ሊከፈል የሚገባውን መስዋእትነት እየከፈለና በችግር እየተፈተነ ጠላቶቹን ድል እያደረገ ቢቆይም በህዝቡ ትከሻ  ተንጠልጥለው ስልጣን ላይ የወጡ የህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች ግን ህዝቡ ይጠብቀው የነበረውን የተሻለ የሰላምና የእድገት ለውጥ አሳጥተው ወደ ከፋው የድህነትና የኋላ-ቀርነት አዘቅት እንዲዘፈቅ በማድረግ ፍዳውን እያሳዩት ይገኛሉ።
    ባሁኑ ግዜ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያነሳቸው የለውጥ ጥያቄዎችና መሰረታዊ ፍላጎቶች ተገቢ ጥናትና ክትትል ተደርጎበት መፍትሄ ከመስጠት  ይልቅ ብሶቱና ጥያቄውን ስላቀረበ ብቻ እንደ ጸረ ልማትና ኣሸባሪ ተቆጥሮ በመጥፎ አይን እንዲታይና እንዲጠረጠር፤ ካዚህ ባለፈም ለስርዓቱ አስጊ የተባለውን ዜጋ በቁጥጥራቸው ስር በማስገባት መሰረት በሌለው የሃሰት ምስክርነት ፍርድ እየተሰጠባቸው ያለበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን።
   የህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች በጭቁኑ የህዝቡ ተሳትፎና ትግል ስልጣናቸው ሊንኮታኮት እየተቃረበ ባለበት ወቅት በዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ማእበል ፈጥሮ ወደ ውድቀት እንዳያመራ ስጋት ላይ ስለሚገኙ ሊካሄድ በታሰበው ስማዊ የምርጫ ዋዜማ ላይ የተለያዩ ቃል እየገቡ ህዝቡን ሊያደናግሩት ቢሞክሩም የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነው ህዝቡ ግን ለህወሃት ኢህአዴግ ባለስልጣናት እድሜ ማራዘሚያ በሆነው አስመሳይ ምርጫ ላይ የሚሳተፍበት እንዳችም ምክንያት የለውም፣ ምክንያቱም ለጭቆናና ለበደል የተፈረደ ህዝብ ላስመሳይ ምርጫ የሚሆን ግዜ ስለማይኖረው።