Thursday, May 21, 2015

የህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች በሽሬና አካባቢው ለሚገኙት የህወሃት የቀድሞ ታጋዮችን ሰብስበው ድርጅታችሁን አድኑት የሚል ስብሰባ ያደረጉላቸው ሲሆን ተሰብሳቢዎቹ ግን እናዳልተቀበሉት ተገለፀ።



    በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን በሽሬና አካባቢው በሚኖሩትና የግል ንሮአቸውን በመምራት ላይ ላሉት የቀድሞ የህወሃት ታጋዮች ግንቦት 8/2007 ዓ/ም የህወሃት/ኢህአዴግ የበላይ ባለስልጣኖች በሆኑት በአባይ ፀሃየ፤ ስዩም መስፍንና ሃለቃ ፀጋይ በርሄ ስብሰባ እንደተደረገላቸው የገለጸው መረጃው የስብሰባው አጀንዳም ደማችሁንና ላባችሁን ያፈሰሳችሁበት ድርጅታችሁ አደጋ ላይ ስለወደቀና የምታደኑትም እናንተ ብቻ ስለሆናችሁ በሚካሄደው ምርጫ ላይ አግዙን የሚል እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
     የቀድሞ ታጋዮች በበኩላቸው ስልጣን ከያዛችሁ በኋላ ስለኛ ያሰባችሁትና የት ወደቃችሁ ብላችሁን የማታውቁት ዛሬ በሁሉም አቅጣጫ ችግር ከደረሳችሁ በኋላ ስልጣናችሁን ለማስቀጠል ስትሉ በምርጫ ዋዜማ ላይ አድኑን ማለታችሁ ትክክል አይደለም፤ እኛ ከህወሃት ክህደት እንጂ ያገኘነው ጥቅም የለም የሚያዋጣንን ነው የምናደርገው በእናንተ እየተታለልን አንኖርም ብለው መልስ በመስጠታቸው እነዚህ ባለስልጣኖች በስብሰባው እፍረት ተከናንበው ያለ ፍሬ መመለሳቸው ተገልጿል።
    በተመሳሳይ ግንቦት 10/ 2007 ዓ/ም በሑመራ ከተማና አካባቢው ለሚኖሩ የቀድሞ የህወሃት ታጋዮች በስርአቱ ካድሬዎች የስብሰባ ጥሪ ቢደረግም ወደ መሰብሰብያ ቦታ የሚሄድ ሰው ስላልተገኘ በሌላ ቀን እንዲካሄድና ጭንቀት የተሞላበት ጥሪ እያደረጉ እንደሆኑ የተገኘው መረጃ አክሎ አስረድቷል።