Saturday, December 29, 2012

በአላማጣ ከተማ ቤታችን አይፈርስም የሚል ከፍተኛ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ታህሳስ 14,2005 ዓ/ም በከተማዋ ኗሪዎች ተካሄደ።





ህዝቡን ሳያማክሩ ከ5500 በላይ መኖሪያ ቤቶችን በግዳጅ በማፍረስ ቦታው ለባለሃብቶች እንዲሰጥ መወሰኑ አምባገነኑ የኢህአደግ ስርዓት በህዝቡ ላይ ያለውን ንቀት ያመለክታል ሲሉ ኗሪዎቹ በምሬት ይገልጻሉ።
በደረሰን ዘገባ መሰረት ቤታቸውን እንዲፈርስ የተወሰነባቸው ሰዎች በከተማዋ ከ 20-30 ዓመታት ለመንግስት ግብር እየከፈሉ ሲኖሩ የነበሩ ሲሆን ምንም ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግና ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጣቸው በ 10 ሽዎች የሚቆጠር ህዝብ በድንገት ከመኖርያ ቤቱ ማፈናቀል በኗሪዎቹ ዘንድ ተቀባይነት ስላላገኘና ተቋውሞሞ ስለገጠመው መንግስት ከከተማዋ ኗሪዎች መካከል የህወሓት አባላት የሆኑትን በመለየት ቅድሚያ ቤታቸውን በማፍረስ ለሌላው አብነት እንዲሆኑ እየገፋፋቸው መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እያለ በከተማዋ ኗሪዎች ተሰሚነት ያላቸው መምህር ሓየሎም ካልአዩ ፤ አቶ ጌታቸው ወልዳይና አቶ ሰለሞን አብረሃ የተባሉ ንጹሃን ዜጎች በስርዓቱ የጸጥታ ሃይሎች የታሰሩ ሲሆን ወ/ሮ ያልጋ ወልደሃና የተባሉ ኗሪም ማስጠንቀቅያ ደርሷቸዋል፣ እንደዚሁም በ 2002 ዓ/ም በተደረገው አወዛጋቢ ምርጫ ህወሓትን ወክለው የቀረቡት አቶ ተሾመ ደርበውንና አቶ ዝናቡ አበበን ህዝቡን ለዓመጽ አነሳስተዋል በሚል ሰበብ ለማሳሰር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ከተበዳዮቹ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
በከተማዋ ቤቶችን የማፍረሱ ዘመቻ ጥሙጋ እስከ ተባለው አከባቢ ድረስ እንደሚሄድ ለማወቅ ተችሏል ።