በደረጃው እጅግ የወረደና ከተገነባም ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረው የሽረ-እንዳስላሰ ሆስፒታል አንድ የጤና ጣብያ
የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት እንኳ በቅጡ መስጠት የተሳነው በቂ የመድሃኒት አቅርቦት ፤ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችንና ባለሞያዎች
ያልተሟሉለት በመሆኑ የአከባቢው ህዝብ እንደድሮው በህክምና እጦት ምክንያት በቀላሉ መፈወስ በሚችሉ በሽታዎች ተሰቃይቶ ህይወቱን
እንደ ዋዛ የሚያጣበት ሁኔታ አሁን ድረስ በተደጋጋሚ እንደሚታይ ከአከባቢው የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
በደረሰን ዘገባ መሰረት በከተማዋ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ካለመኖር ጋር ተያይዞ የሚመጡ የውሃ ወለድ
በሽታዎችንና ተገቢ የጤና አገልግሎት መስጠት የሚችል በሆስፒታል ደረጃ ሊገለጽ የሚችል የጤና ተቋም ባለመኖሩ ምክንያት በአከባቢው
እየታየ ያለው የህክምና አገልግሎት እጦት ክፉኛ የተማረረው የከተማው ኗሪ ህዝብ ችግሩ በሚመለከተው አካል ታይቶ አስፈላጊውን ትኩረት
እንዲሰጠው በተወካዮቹ በኩል በተደጋጋሚ ከዞን እስከ ክልል ላሉ የመንግስት ባለስልጣናት አቤቱታውን ቢያቀርብም እስካሁን ድረስ የተሰጠው
ተጨባጭ መላሽ የለም።
ይህ በእንዲህ እያለ የሆስፒታሉ አስተዳዳሪ አቶ መሓመድ በበኩላቸው ከአከባቢው ህዝብ እየቀረበ ያለው የህክምና
አገልግሎትን የተመለከተ ቅሬታ ትክክለኛና ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ቀደም ብሎ መፍትሄ ማግኘት የነበረበት አንገብጋቢ ጥያቄ ነው በማለት
ከህዝቡ ተወክለው ለተላኩት ተወካዮች መግለጻቸው ለማወቅ ተችለዋል።