Thursday, March 20, 2014

በትግራይ ክልል ደረጃ ከየካቲት 5 እስከ የካቲት 16 /2006 ዓ/ም ድረስ በውቅሮ ከተማ ለተካሄደው የስፖርት ውድድር ተብሎ የተመደበው በጀት በባለ-ስልጣናት በመጠፋፋቱ ምክንያት ስፖርተኞቹ ቅሬታቸው እንደገለፁ ታወቀ።



እነዚህ ከሁሉም የትግራይ ወረዳዎች የመጡና የተሻለ የስፖርት ውጤት ያላቸው ተወዳዳሪዎች ለመለየት ተብሎ በውቅሮ ከተማ ሲካሄድ እንደሰነበተ የገለጸው መረጃው በውድድሩ ወቅት የተሸነፉት ወረዳዎች ገና አጠቃላይ የውድድሩ ይዘት ሳይፈጸም በጀት የለንም ወደ ቦታቹህ ተመለሱ በመባላቸው ምክንያት መጥፎ ስሜት ውስጥ መግባታቸው ተገለጸ።
    ሲካሄድ ለቆየው ስፖርታዊ ውድድር ተጀምሮ እስኪጨረስ ድረስ በቂ በጀት የተመደበለት ቢሆንም የውድድሩ አዘጋጆች የሆኑ አስተዳድሪዎች ግን ለስፖርተኛው ተብሎ የወጣው ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው ምክንያት ከአሰልጣኞች በስተቀር በውድድሩ ወቅት የተሸነፋቹህ ወደየ ቦታቹህ ሂዱ ብለው ላቀረቡት መመርያ ወጣት ስፖርተኞቹ ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም ስለምንፈልግ ውድድሩ ሳይጨረስ አንሄድም በማለት በራሳቸው ፈቃድ ከግል ኪሳቸው ለሆቴል አልጋና ምግብ ወጪ አድርገው ቢቆዩም በስተመጨረሻ ግን ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ ስለ ሆነባቸው ቅሬታቸው ለባለስልጣናቱ እንደገለፁ ለማወቅ ተችለዋል።
    ይህ በእንዲህ እንዳለ ተወዳዳሪዎቹ በወቅቱ ላጋጠማቸው በደል መፍትሄ እንዲደረግላቸው በማለት ወደ ሚመለከታቸው የክልል ባለስልጣናት ብሶታቸው ቢያቀርቡም ሰሚ ጀሮ ባለማግኘታቸው ምክንያት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄደው የስፖርት ውድድር የቅርብ ተጠሪና ሃላፊነት የሚወስድ አካል የሌለው ነው ሲሉ በክልሉ ውስጥ ላለው ብልሹ አሰራር እንዳወገዙት መረጃው አስታውቀዋል።
    በተመሳሳይ መንገድ በመቐለ ከተማ ከ 1999 ዓ/ም ጀምሮ ደረጃውን የጠበቀ ስታድዮም መስርያ እየተባለ ከህዝቡ እየተዋጣ ለቆየው በርከት ያለ ገንዘብ በአካባቢው ባለስልጣናት እየተመዘበረ በመሆኑ ምክንያት መሰራት የነበረው የስታድየሙ ክፍል መዘግየቱና ስፖረተኞቹ የስፖርት ማዘውተርያ ቦታ አጥተው ከአያሌ የስፖርት ልምምዶችና ውድድሮች ተሰናክለው እንደሚገኙ ከከተማው የተገኘው መረጃ አክሎ አስረድተዋል።