Saturday, March 15, 2014

ኢሮብ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ የስርአቱ አስተዳድሪዎች ለአካባቢው ህዝብ በመሰብሰብ መብታቹህ ሊከበር የቻለው በህወሃት ኢህአዴግ መንግስት ነው ብለው ላቀረቡት ሃሳብ በህዝቡ ተቀባይነት እንዳላገኘ የተገኘው መረጃ አስታወቀ።



በመረጃው መሰረት በስብሰባው ላይ እንደ መወያያ ርእስ ሆነው የቀረቡ አጀንዳዎች የኢሮብ ብሄረሰብ መብቱን ተጠብቆ ልጆቹ በእናት ቋንቋ እንዲማሩ፤ ህዝቡ ቋንቋውን ተጠቅሞ ራሱን በራሱን እንዲያስተዳድር፤ ፍትህ እንዲያገኝና የሚያስፈልገው መረጃ ለማግኘት በቋንቋው የሚድያ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን፤በአጠቃላይ መልካም አስተዳደር በመረጋገጡ ምክንያት የህብረተሰቡ እድገት ተሻሽለዋል በስርአቱ ተላላኪዎች እንደተነገረና፣ ይበልጥ የህወሃት ኢህአዴግ ስርአት ትግራይ ውስጥ ከሚገኙ ብሄረሰቦች ለኢሮብ ብሄረሰብ ልዩ ትኩረት ማድረጉና ህዝቡም ከስርአቱ ጎን ቆሞ ሌሎች ድርጅቶችን መቃወም እንዳለበት የሚያሳስቡ አጀንዳዎች እንደነበሩ መረጃው አክሎ አስረድተዋል።
    ይህ በእንዲህ እንዳለ በአካባቢው አስተዳዳሪዎችና ካድሬዎች ለቀረቡ ሃሳቦች በመቃወም በህዝቡ የቀረቡ ጥያቄዎች፣-
-    መንግስት ከአቅማችን በላይ ማዳበርያ እንድንገዛ አስገዳጅ ትእዛዝ እየሰጠን ነው፤
-    ማንኛውም ሰው በሰራው ልክ ይከፈለዋል ብላቹህ ስታበቁ ህዝቡ የእለት ጉርሱ ለሟሟላት ሲል ከደውሃን ወደ አራዕ የሚወስደው መንገድ ሌትና ቀን ከሰራ በኋላ ገንዘቡን ከለከላቹሁት፤
-    በቤተሰብ ትስስርና በጥቅም በመደለል ለግለሰቦች መሬት እየተሰጠ ነው። ይህ ህጋዊነት ያልተላበሰ አሰራር መንግስት ለምን አልተቆጣጠረውም፤
-    የንፁህ ውሃ እጥረት በወረዳዋ ውስጥ አለ። በተለይ በጎራንጎይራ አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ለአመታት ያህል በዚሁ እጥረት እየተሰቃየና እንስሳውና ሰው በአንድ ላይ ከአንድ ምንጭ እየተገለገለ ባለበት ሁኔታ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ለምን አላደረገም፤
-    መንግስት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን አድርጌአሎህ እያለ በሚዋትትበት በአሁኑ ሰአት ለድሃው ህብረተሰብ ተብሎ የመጣው የእህል እርዳታ በወረዳዋ የሚገኙ አስተዳዳሪዎች ለይምሰል ሰጥተናል ለማለት የተወሰነ ካከፋፈሉ በኋላ አብዛኛው ለራሳቸው ይጠቀሙበታል ይህ ለምን ቁጥጥር አልተደረገለትም።
-    አብዛኛው ከ35 ሺ በላይ የሆነው የኢሮብ ብሄረሰብ ህዝብ። በ7 የተለያዩ ገጠሮች ተበትኖ እንደሚገኝና ያካባቢው አስተዳደር በፈጠሮው ችግር ሳቢያም ማህበራዊ ኑሮውን ከግዜ ወደ ግዜ እየከፋ በመሄዱ ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሚገልፁ ጥያቄዎችና ሌሎች የተቃውሞ ሃሳቦች እንደተነሱ ለማወቅ ተችለዋል።