Saturday, November 29, 2014

የኢህአዴግ መስመር የህዝቡን መብት አያረጋግጥም!!



    የህወህት ኢህአዴግ አመራሮች የሚከተሉትን መስመርና አላማ ከሚገባው በላይ እያራገቡና እያብለጨለጩ በወረቀት ላይ ከሚፅፉትና ከሚያስተጋቡት በስተቀር ተግባር ላይ ምንም አይነት ትርጉም ያለው ለውጥ የማያመጡ መሆናቸውን ባለፍት 23 የስልጣን ግዝያቶች ተረጋግጧል።
    ይህ ስርአት ህገ መንግስት ላይ እስፍሬዋለሁ በሚላቸው ለማስመሰል ብቻ የተቀመጡት ድንጋጌዎች፤ ደንቦች፤ ህግና ስርአቶች የህዝቡን መብት እንዳላስከበሩ፤ ሁሉም ያገሪቱ ህዝብ ህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጡት አንቀፆች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዳልተከበረ፤ ስርአቱም ቢሆን በረቀቀው ህገ መንግስት መሰረት ተገዢ ሆኖ እንደሚሄድ አድርጎ እራሱ  ቢገልፅም መሬት ላይ ያለው ሃቅ ግን ከሚሰራው እውነታ ጋር በእጅጉ እንደማይገናኝ ብዙ ግዜ ተነግሮለታል።
    የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት የህዝብን መብት የማያስከብር፤ ፍትሃዊ አሰራርን የማይከተል፤ በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የተጨማለቀ፤ እድልዎና ወገናዊነት እንደ ልማዳዊ አሰራሩ አድርጎ የሚጠቀም፤ በአጠቃልይ አፋኝና ፀረ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚጓዝ ቡድን መሆኑ ከመጀመርያም ቢሆን የሚታወቅ እንደሆነና አሁንም በተጠናከረ መንገድ እየቀጠለበት መሆኑን የሚያሳይ የሰሞኑን ተግባሮች እንይ።
Ø  ከ 2007 ዓ/ም ምርጫ ጋር ተያይዞ በተለይ ያስጉኛል ለሚሏቸው የተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት በተለያየ መንገድ እንዲዳከሙ ለማድረግ አጠናክሮ እየተንቀሳቀሰበት መሆኑና ሰሞኑን በትግራይ ክልል፤ ዳንሻ በተባለው አካባቢ የአንድነት ድርጅት አባላት ህዝቡን ሰብስበው ቅስቀሳ እያካሄዱ በነበሩበት ግዜ በህዝቡ ተቀባይነት ስላገኙ በወያኔ ካድሬዎች ተይዘው እንደታሰሩና አድራሻቸው እንዲጠፋ መደረጉ፤
Ø  በዓብይ ዓዲ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የስርአቱ ካድሬዎች ለአረና ትግራይ ድርጅት አባላት ፓንፕሌት አስራጫችሁ በሚል ሰንካላ ምክንያት ፖሊሶችን በማሰማራት አስረው እያሰቃዩዋቸው መሆናቸውንና ካሁን በኋላ ማንኛውም ሰው ተቃዋሚዎች በሚጠሩት ሰብሰባ ላይ እንዳይገኝ ጥብቅ መመርያ መሰጠቱ፤
Ø  የስርአቱ የመከላከያ ከፍተኛ ባለ ስልጣኖች በህዝቡ ሃብት ለስራ ተብሎ የተገዛውን ነዳጅና ሌሎች ንብረቶች እየሸጡ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት መሆናቸው፤ በዚህ መሰረትም ብርጋዴር ጀነራል ጀማል መሓመድ ብርሃን ወይ (ወዲ ጎጀላ) በሚል ስም የሚታወቀው ከፍተኛ የወታደር አመራር  ለስራ ማስኬጃ ተብሎ የተረከበውን አንድ ቦቴ ነዳጅ በሙሉ ሽጦ በመቶሺ የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ግል ጥቅሙ እንዳዋለው፤
Ø  በአባይ ግድብ ውስጥ ለበርካታ ወራቶች በማህበር ተደራጅተው ሲሰሩ የቆዩትን ሰራተኞች አሰሪያቸው የሆነው የመከላከያ ኮንትራክተር በገባላቸው ውል መሰረት ሂሳባቸውን መከልከሉ፤
Ø  የ7 ዓመት አገልግሎታቸውን የጨረሱ ወታደሮች አሰናብቱን ብለው ቢጠይቁም የስርአቱ ባለስልጣኖች ግን ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ ሌላ የማታለያ ቅስቀሳ በማካሄድ አስገድደው  እንደገና ለ7ዓመት እንዲቆዩ ማድረጋቸው የሚሉና ሌሎች ይገኙበታል፣ 
  የስርአቱ ተግባርና ተጨባጭ እውነታ ይህ እያለ ታድያ ለምን ይሆን ነጋ ጠባ የህዝቡ ፍትህና መብት መከበርን አስመልክቶ በተለያዩ መድረኮች ርእሶችን እያነሳ ፕሮጋንዳውን የሚነፋ ከተባለ ግን ቀጥታዊ መልሱ የራሱን ህዝብና የአለምን ማህበረሰብ በማደናገር የስልጣኑን እድሜ ለማራዘም ተብሎ እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም፣
    ስለዚህ! ይህ ኢ-ፍትሃዊና የህዝቡን መብት እየረገጠ ያለው ስርዓት እስከ ዘላለሙ ከአገራችን ለማራቅ ገና ወደ ስልጣን ሲወጣ ጀምሮ እየተጠቀመበት በቆየው ወርቃማ ቃላቶችና አስመሳይ የመብት ተጠቃሚነት ሳንደናገር  ትግላችንን ማጠናከር ይገባናል፣ ምክንያቱም የህወሃት ኢህአዴግ መስመር የህዝቡን መብት ማረጋገጥ ስለማይችል፣