Friday, February 13, 2015

በኢህአዴግ ገዥው መንግስት አካሄድ ግፍ የደረሰባቸው በጦርነት የተጎዱ የትግራይ ተወላጆች ህብረተሰቡ ካለፉት ምርጫዎች ተምሮ የሚያዋጣውን ፓርቲ መምረጥ አለበት እያሉ በመቀስቀስ ስራ ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ።



  ምንጮቻችን የለኩልን መረጃ እንደሚያመለክተው።- የደርግን ስርዓት ከስልጣን ለማስወገድ በተካሄደው የ17 አመት ትግል አካላቸውን ሰንክለው ያለምንም እገዛ የተጣሉ የትግራይ ተወላጆች ለ24 አመታት ያህል በተደራራቢ የማህበራዊ ችግር እየተሰቃዩ በነበሩበት ሰዓት አንዳችም የስርዓቱ ባለስልጣን እንዳላያቸው የተማረሩት እነዚህ በጦርነት አካላቸው የተጎዱ ወገኖቻችን አካላችንን ሰንክለን ምን ያገኘነው ነገር አለን ከሰው በታች ሁነን እየኖርን እንገኛለን ስለዚህ አሁን እየተካሄደ ባለው አስመሳይ የማይተገበር ቃል ሳትደናገሩ ሓቀኛና የሚያዋጣችሁን ድርጅት ምረጡ እያሉ ለህብረተሰቡ በማነሳሳት ላይ እንደሚገኙ ሊታወቅ ተችሏል።
  የተጎዳ አካላቸውን እያሳዩ ለህዝብ በመቀስቀስ ላይ መሆናቸውን የተመለከቱ የህወሃት ኢህአዴግ ባለስልጣናት በጥር 14 /2007 ዓ.ም ከያሉበት ቦታ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ እንደጠሯቸው የገለፀው ይህ መረጃ ስብሰባውን እንዲመራ የተመረጠው አስመላሽ ወልደስላሰ የተባለ ባለስልጣን ደግሞ እኔ እንደናተ አካለ ስንኩል ነኝ ድርጅታችን አሁን ሁኔታችሁ መረዳት ስለፈለገ ነው የጠራችሁ እስካሁን እንደዚህ አይነት ያላደረገበት ደግሞ ሁሉም ነገር በመለስ የሚጨረስ ነገር ስለነበር ነው በሚል አነጋገር ላነሱት ጥያቄ ለመሻፋፈን ይሞክር እንደነበር የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
  ቢሆንም ግን ተሰብሳቢዎቹ አንተ የጦርነት አካለ ጎደሎ ብትሆንም የምክር ቤት አባል ተብለህ በተመቻቸ ህይወት ነው እየኖርህ ያለኸው እንዳንተ አይነት ኑሮ ብንመራ የሚያናግረን ነገር ባልነበረ በማለት የነበረውን ስብሰባ ረግጠውት እንደወጡ ለማወቅ ተችሏል።