በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የከፋና ህይወትን
እንደቅጠል እያረገፈ ያለበት ደረጃ ላይ ይገኛል። በአገሪቱ በዘግናኝነታቸው ከሚታወቁት የድርቅ ዘመናት፣ የ1977 ዓ.ም እና የ1965
ዓ.ም የረሃብ አደጋዎች ቢሆኑም ዘንድሮ በኢልኒኖ ሳቢያ የተከሰተ ተብሎ የሚነገረው የረሃብ ቸነፈር ግን በኢትዮጵያ ምድር ላይ ከማንኛውም
ጊዜ በከፋና ሁሉንም አካባቢ በማዳረስ ከድርቅ ችግርነቱ አልፎ ለረሃብ ውርጅብኝና እልቂት የዳረገ ቸነፈር ሁኗል።
መቸም የኢትዮጵያ መሬት በውሃ ችግር ምክንያት የህይወት ማስቀጠያ የሚበላና
የሚጠጣ ጠፋ ተብሎ እጅን ዘርግቶ ከውጭ አገራት መለመን፣ ለሰሚው ግራ ነው ብለን እንለፈው። ምክንያቱም የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው
ሲባል ማን ያምናልና።
ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተላችን ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት
አስመዝግበናል፥ ገበሬው ከእለት ጉርሱ አልፎ በስልጣኔ ጣራ ላይ በመረማመድ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆኗል፣ የተባለለት የአገራችንን ህዝብ
የኑሮ ሁኔታ እውነቱ ሲመሰክር ግን የአንድ ወር ጉርሱን እንኳን ከማየሸፍንበት ደረጃ ላይ ነው ያለው።
ይህም የአገራችን ህዝብ የድህነት መንስኤ የኢትዮጵያ መሬት አላበቅል
ብሎ ወይንም ደግሞ የኢትዮጵያ መሬት ውሃ አጦም አይደለም። ግብርናውን ለማሳደግና ለመለወጥ የተነደፈ እስትራቴጂና ፖሊሲ ስለሌለ
እንጂ፣ የኢህአዴግ የኢኮኖሚ አቅጣጫ የአገርን ህዝብ ማዕከል ባለማድረጉ የተነሳ፣ እነሆ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት ወለል
በታች ለረሃብ አደጋ ተጋልጦ ይገኛል።
የገዢው ቡዱን አመራሮች በገዛ ሚዲያቸው ዓይነ ካሜራ እየቀረፁ፣ ህዝብንና
የውጩን አለም ለማደናገር የሚጠቀሙበት የማደናገሪያ ስልት እና የእርሻ ልማት፣ ለማን እንደሆነ የሚጠፋው ሰው አይኖርም። የኢህአዴግ
ባለስልጣናት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ለውጭ አገር ባለሃብቶች የሸጡት
የአገራችን ህዝብ የበይ ተመልካች የሆነባቸው ቦታዎች በመሆናቸው።
በድብልቅ ግብርናና በአርብቶ አደርነት የሚተዳደረው የአገሪቱ ህዝብ
ቁርኝቱ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ከሰማይ ደመና ጋር ብቻ በመሆኑ በረሃብ አለንጋ ሲገረፍ ቆይቷል። አሁንም የተሻሻለ ነገር የለም፣ ምክንያቱም
አገሪቱን በየጊዜው የመሩት ገዥዎች፣ ድሃውን ህዝብ ከአፉ ሞጭቀው ማስገበር እንጂ ኑሮው በየትኛው መንገድ ቢጠቀም የተሻለ ለውጥ
ያመጣለታል ብለው አስበውበት ስለማያውቁ ነው።
አሁንም በዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን የኢትዮጵያ አርሶ አደር ገበሬና አርብቶ
አደር፣ ዝናብን የጠበቀ በመሆኑ ለዚህ ዛሬ ለተከሰተው የረሃብ እልቂት በዓይናችን ክፉ ቀንን እንድናይ አድርጎናል። አርሶ አደሩ
ከልጆቹ አብልጦ የሚወዳችው ከብቶቹ በግጦሽ እጦትና በውሃ ጥም ፊቱ ላይ ረግፈውበታል። ልጆቹንም በረሃብ ተነጥቋል።
ህዝቡ በዚህ አስከፊ የረሃብ ቸነፈር ተውጦ እያለ፣ መንግስት ፈጥኖ
አልደረሰለትም። አሁንም ቢሆን በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተፅዕኖ እንጂ መንግስት በእውነት ከልቡ በመነጨ ለኢትዮጵያ ህዝብ አላዘነለትም።
ይባስ ብሎ ከውጭ አገራትና የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የሚላከውን የህይወት
ማዳኛ እርዳታ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ወደየግል ኪሳቸው ማዛወራቸው ነው። በረሃብ ለተጎዱት የተላከውን ገንዘብ ቪላቸውን ሲገነቡ፣
በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ምን ያክል ንቀት እንዳላቸው ያሳያል። ይህ ግፍና ብዝበዛ ኢህአዴጎዎች ከቀደሙት ጨቋኝ መሪዎች ከደርግና ከኃይለ
ስላሴ የወረሱት ስለ ህዝብ ምንም ዓይነት ሃላፊነት አለመሰማት ነው።
ንጉስ ኃ/ሥላሴ በ1965 ዓ.ም ህዝብ በረሃብ እየረገፈ ለአፍሪካ ህብረት
ፈንጠዝያቸው በማሸብረቅ፣ የውጭ መንግስታትን ያዝናኑ ነበር። እርሳቸውም ህዝቡን ንቀው ደቅድቀው፣ የውጭ አገራትን ሚሊዮናት ገንዘብ
እያወጡ ለግል ህይወታቸው ይንሸራሸሩ ነበር።
ይህ ድርጊት ዛሬም ድረስ አልበቃ ብሎ፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከውጭ
መንግስታት ጋር ሲገባበዙና የግል ገንዘባቸውን በየውጭ ባንኩ ሲያካብቱ፣ ይታያሉ። ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ልክ በቀድሞዎቹ
ጨቋኝ መንግስታት ሲፈፅሙት የነበረውን ግፍና በደል በመውረስ፣ እነሆ
በሃገሪቱ ሃብትና በህዝብ ገንዘብ እንደፈለገው ከሩቅ ምስራቅ እስከ ምዕራብ አፍሪካ ለሳምንታት ሞግዚቶቹንና አሽከሮቹን አስከትሎ
እየተንሸራሸረ ይገኛል።
ጭቁኑና ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን፣ በረሃብ
እየተሰቃየ መሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ አልታያቸው ብሎ ሳይሆን፣ ህዝባዊ ኃላፊነት ስለማይሰማው ነው። በማን አለብኝነት ከህዝብ ይልቅ
የግሉን ሽርሽር ያስቀደመው፣ በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ በረሃብ እልቂት እየተሰቃየ ራስ ወዳደቹ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ግን የአገራችን
እንጡራ ሃብት እየዘመቱ ለግል ኑራዋቸዉን ስራራጡ ይታያሉ።
No comments:
Post a Comment