Friday, April 22, 2016

ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ት.ህ.ዴ.ን) የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ




በገዥው ስርዓት ኢህአዴግ ቡድን ስር የወደቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ለህይወቱ ዋስ የሚሆነው አካል ባለማግኘቱ ከውስጥና ከውጭ በሚመጡ ኃይሎች ህይወቱ እየተቀጠፈ ሌት ተቀን በፍርሃትና ረአድ እየኖረ እንደመሆኑ የሚጠፋው ወገን የለም፣ አንድ በስልጣን ላይ ያለ መንግስት እየመራሁት ነው የሚለውን ህዝብ በሰላም ወጦ በሰላም እንዲገባ ዋስትና መስጠት ግዴታው ቢሆንም እንኳ። ከህዝብ ተቀባይነትና እምነትን ያጣው በስልጣን የሚገኘው ገዥው ስርዓት ኢህአዴግ የዜጎችን ህልውና ሊታደግ ህዝባዊ ሃላፊነትም ይሁን ሃገራዊ ስሜት ስለሌለው ዜጎቻችን  ጨካኝ ክንዳቸውን በሚዘረጉ ሃይሎች ሲገደሉና ታፍነው ሲወሰዱ እየታዘብን ነው፣
     የተከበርህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ፦በእነዚህ ባለፉት የቅርብ ዓመታት እንኳ ስንመለከት ዜጎቻችን በየሔዱበት ሲጨፈጨፉና እንደ እባብ ሲቀጠቀጡ ማየት የተለመዱ ድርጊቶች ሆነው አልፈዋል፣ ለምሳሌ ሩቅ ሳንሄድ በ2007 ዓ/ም በሊቢያ ከ30 በላይ ዜጎቻችን እንደ ፍሪዳ በግ ሲታረዱ ይተመለከተ ሰብዓዊ ፍጡርን ሁሉ የደም እንባ ያስለቀሠ ብቻ ሳይሆን ዓለምን በሙሉ አሳዝኖ ያለፈ ፍፃሜ መሆኑ የትናንትና ትውስታ ነው፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ዓ/ም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎቻችን በሥራ ቦታቸው ላይ በእሳት ቋያ ተዳፍነውና ተሰቃይተው ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።
    በየመንም ቢሆን በ2007ዓ/ም በአገሪቱ ባጋጠመው ውስጣዊ ቅልውላው ዜጎቻችን ህዝቦቼ ብሎ ተሯሩጦ የሚያወጣቸው መንግስት አጥተው በጣም ብዙ ሴቶችና ህፃናት የሚገኙባቸው በማይመለከታቸው የእሳት እረመጥ ተንገብግበው አልቀዋል። ከሁኔታው በኋላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የመናውያን አገራቸውን ትተው ወደ ኢትዮጵያ ሲሰደዱ በተቃራኒው ኢትዮጵያውያን ዜጎች ግን በአምባገነኑ ኢህአዴግ እጅ ከምንገባ እዚሁ መሞት ይሻለናል በማለት ሲተርፉ ታይተዋል፣ ይህም አገራችን ኢትዮጵያ ለባዕዳን ገነት ስትሆን ለዜጎቿ ደግሞ ገሃነም መሆኗን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን እውነታ ነው፣
    በሰው አገር ከምንሞት በአገራችን መሞት ይሻለናል በማለት ወደ አገራቸው ሊመለሱ የፈለጉትንም ቢሆን ተቆርቁሮ ወደ አገራቸው የሚመልሳቸው አካል ባለማግኘታቸው ሊመለሱ አልቻሉም፣ የማደናገር እከይነት የተጠናወተው ገዥው ስርዓት ኢህአዴግ የመን ውስጥ ይቀመጡ ከነበሩት በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩት ኢትዮጵያውያን ከአርባ የማይበልጡትን መልሶ ለፖለቲካዊ ሸቀጥ ብቻ ሲጠቀምባቸው ታይቷል፣ እነዚህ በሊቢያ በየመንና በደቡብ አፍሪካ የተቀጠፉትና  የተሰቃዩት ኢትዮጵያውያን በአንድ ዓመተ ምህረት ውስጥ የተፈፀሙትን እንደምሳሌነት ለመጥቀስ ያክል እንጂ በሳውዲ አረቢያና በሌሎችም አገሮች ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ደማቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩትን ንብረታቸውን በአንድ ጀምበር ሲወድምና በአሰቃቂ ግርፋት የሚማፀኑትና የሚያልፉት የስቃይ ጊዜ የሚረሳ ድርጊት አይደለም።።
     የተከበርህ የኢትዮጵያ ህዝብ ፦ ሰሞኑን ደግሞ በጋምቤላ ክልል የሚኖሩ ህዝቦቻችን በደቡብ ሱዳናውያን ታጣቂዎች በተፈፀመ አሰቃቂ ጥቃት ከ200 በላይ ወገኖቻችን ተገድለው ፤70 የሚሆኑ ቆስለው ፤ ከ100 በላይ ታግተው ሲወሰዱ ፤በርካታ ቤቶች ተቃጥለውና በሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶቻቸው ተዘርፈው ሲነዱባቸው አለሁላችሁ ብሎ የሚያድናቸው መንግስታዊ ኃይል አልተገኘም፣
     የገዥው ስርዓት ጠቅላይ ሚኒስቴር ግን ድርጊቱ በተፈፀመ በነጋታው በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ የአዞ እንባ ሲያነባ ታዝበናል፣ ዘመናዊ ሠራዊት ገንብተን ከአገሩ አልፎ ለሌሎች አገሮች በሰላም አስከባሪነቱ ቀዳሚ ሆነናል ያሉለት በተግባር ሲታይ ግን ለዚህ ደቡብ ሱዳናውያን የአገራችንን ድንበር ጥሰው በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንኳን ሊከላከል የሚችል ኃይል በቦታው አልተገኘም፣
    ህዝባችን የጋምቤላ ህዝብ ከአለፈው አመት ጀምሮ በደቡብ ሱዳናውያን ጥቃት ሲደርስበት  እንደቆየ ኃይለማርያም ደሳለኝ በልሳኑ በአጋጣሚው ተናግሯል፣ በትኩረት ሊታይ የሚገባው ነገር ግን ችግሩ መኖሩን እያወቁ ችግሩ ለምን አልተፈታም? ለህዝቡ ጠበቃ የሚሆን ሰራዊትስ በአካባቢው ለምን ሳያሰማሩ ቆዩ የሚለው ሊመለስ የሚገባው ቀንድ ጥያቄ ነው፣
    ገዥው ስርዓት ኢህአዴግ በደቡብ ሱዳን ብቻ ሳይሆን በሱዳን ሰራዊትም ጭምር ህዝባችን እየተገደለና ያካበተው ሃብት እየተቃጠለ ዓመታት አስቆጥሮ እያለ ዕድሜ ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ሊናገር አለመቻሉ የከዳተኛነቱ ምስክር ከመሆን አልፎ ሌላ ትርጉም ሊሠጠው አይችልም፣
     በተለያየ ጊዜ ይህን በአገሮች መካከል ያለውን ውስጣዊ ቅሬታ የሌለ ለማስመሰል ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በሚል። ትርጉም በሌላቸው የላይኞቹ የስርዓቱ ካድሬዎች የሚመራ ልኡክ እየሰደዱ ዲፕሎማሲያችን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ፥ ከመንግስታቱ ግንኙነት በዘለለ የህዝቦች ግንኙነት ተጠናክሮ ይገኛል እያለ ነጋ ጠባ ሲለፈልፍ ይሰማል፣ ዲፕሎማሲ ባላት አገር ግን ዜጎች በየሄዱበት ሊታረዱ ምክንያታዊ ባልሆነ ነገር በአገራቸው እያሉ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ሊፈፀምባቸው አይችልም፣
    ለማጠቃለል የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ድርጅት ይህንን መግለጫ ሲሰጥ በንፁኃን ወገኖቻችን በጋምቤላ ህዝቦች ላይ በተፈፀመው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልፃል፣ ይሄንን እኩይ ተግባር የፈፀሙትን ኢ-ሰብዓዊ ኃይሎች ደግሞ አጥብቆ ይኮንናል፣ይህ በህዝባችን ላይ ተፈፅሞ ያለው ጭፍጨፋ ተጠያቂው ደግሞ ገዥው ስርዓት ኢህአዴግ እንደሆነ ደጋግሞ ያረጋግጣል፣

የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ሚያዝያ 2008 ዓ/ም

No comments:

Post a Comment