Friday, May 6, 2016

ዘላቂ የዜጎች ዋስትና ዘላቂ መፍትሔ ሲኖር ነው!!



 የአንድ አገር እድገት ይሁን ለውጥ ተግባራዊ የሚሆነው የዜጎችን ዋስትና በማረጋገጥ ዘላቂነት ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ ሲሰፍን መሆኑ ጥያቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም።ምክንያቱም ያለዋስትና ሰላምና ዴሞክራሲ ማንኛውም እንቅስቃሴ ውጤታማ ሊሆን ስለማይችል።
    ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ለውጥና እድገት አሰራር ወሳኝ ተሳትፏቸውን የሚያረጋግጡት በድንገት ሳይሆን በየዕለቱ የሚያሰቃዩአቸውን ማሕበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ህገመንግስታዊ መብታቸውን በሚገባ  ተገንዝበው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በማካሄድ ዘላቂ ዋስትና በማግኘት ለጋራ ጥቅማቸው እንዲቆሙ ሲደረግ ነው።
    ለዚህ ደግሞ ውስጣዊ አንድነታቸውን በማረጋገጥ በነፃ ህሊና የተመሰረተ ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውንና እኩልነታቸውን በአስተማማኝነት በመጨበጥ በየጊዜው እየዳበረ የሚሄድበትን አቅጣጫ በመከተል ብቻ ነው የሚረጋገጠው።ይሁን እንጂ ሁሉንም መብቶችና ተቀጣጣይ የህዝብ ጥያቄዎች በማፈን በዜጎች መካከል ውስጣዊ ቅሬታዎችንና ግጭቶችን ሁልጊዜ እያየ ብቁ ምላሽና ዘላቂ መፍትሄ የሚያስቀምጥ ስርዓት ወይም መንግስት ከሌለ ደግሞ ይረጋገጣል ትብሎ ተስፋ የሚሰጠው አይደለም።
     በመሆኑም የኢህአዴግ ባለስልጣናት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ለሩብ ክ/ዘመን ይህል የፈጠሩት አውዳሚ ፖሊሲና የሙስና አስተዳደር በብሄር ብሄረሰቦች መካከል እየተፈጠሩ የመጡና ያሉ ተቀጣጣይ ችግሮች ሊፈታቸው አልቻለም ብቻ ሳይሆን ዜጎቻችን እያጋጠማቸው ካለው አደጋ ለመዳን ከጎረቤት አገሮች መጠለያ እንዳያገኙ በተለያዩ የአገራችን የተፈጥሮ ሃብቶች እየተሸጡ በጊዜያዊ ወልጋዳ የእድሜ ስልጣን ማራዘሚያ መሰረት ያደረጉ ሽፍን የበስተጀርባ ውሎች እየተፈፀሙ ንፁሃን ዜጎች ከገቡበት እየታደኑ ለወያኔ ኢህአዴግ የሰንሰለት ችንካር አሳልፎ ለመስጠት እየተደረገ ያለው ሴራ የሚታወቅ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን የመዋሰኛ ድንበሮች በየጊዜው የሚነሱ ቅራኔዎችና ግጭቶች መፍትሄ ሳያገኙ በየጊዜው እየተነሱ የዜጎቻችን ህይወት እንዲቀጠፍና እንዲጨፈጨፉ ማድረግ የስርዓቱ ቀንድ ተግባር ሆኖ ይገኛል።
     የዚህ ውጤቱ ደግሞ በጋምቤላ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ መቅሰፍት ሲሆን በተመሳሳይም በሰሜን ሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል መደምደሚያ ያልተደረገለት ንትርክ ቀጣይ በወገኖቻችን ላይ የሱዳን ወታደሮች በህይወትና በንብረት ላይ ከባድ አደጋ እያወረዱ የመጡበትንና  ያሉበትን ሁኔታ ሁሉም የሚያውቀው ሃቅ ነው። 
     በዚህ መሰረት የአገራችን ህዝቦች በአገራቸው የተረጋጋ ሰላም ፤ፍትህ፤ነፃነት፤ስራ፤ዴሞክራሲና ዋስትና ያለው ህይወት አጥተው  ባልፈለጉት አገር እየተሰደዱ እንደ ጅግራ ጫጩት የሚንከራተቱት ተገደው ብቻ ሳይሆን በየሄዱበት እየተጎሳቆሉ አሰቃቂ ግርፋት ስቃይና ሞት እየተፈፀመባቸው መጥተዋል።ዛሬም ከ70በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ከታንዛንያ ወደ ኬንያ በህገወጥ መንገድ የገቡ ተብለው በባዕዳ አገር ሲበተኑና ሲወረወሩ የደረሱበትን መንግስት ተጠይቆ የማውቀው ጉዳይ የለም ሲል መንግስት አለ ከማለት አገራችን መንግስት አልባ ናት ብሎ ለመግለፅ የሚያሻማ ነገር የለውም።
    ስለዚህ በወያኔ ኢህአዴግ የዜጎች መብት ሊከበር በተሰደዱ ወገኖች ላይ የሚደርሰው ስቃይና እልቂት እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚፈጠሩ ቅራኔዎች በህዝባችን ላይ እየደረሰ ካለው ጥቃት ለመዳን ዋስትና ያለው ዘላቂ መፍትሄ ወደጎን በመተው ጊዜያዊ ምልጃና ትናንሽ ቀዳዳዎችን ለመሸፈን መሯሯጥ መፍትሄ ሊሆን አይችልም።
    ምክንያቱም የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት  ህዝቦች አንድነትና ስምምነት በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነት መልካም ጉርብትናና ዕድገት ለማምጣት በጋራ እንዲቆሙ የሚያደርግና የሚያበረታታ ሳይሆን በአንጻሩ እርስ በርሳቸው እንዲበጣበጡና አንድነታቸው ፈርሶ ዜጎቻችን ከጎረቤት አገሮች ጋር ስምምነትና ፍቅር አጥተው መጠለያ ቦታ እንዳያገኙ ለማድረግ የቆመ ስለሆነ።

No comments:

Post a Comment