Sunday, August 14, 2016

ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) የተሠጠ ድርጅታዊ መግለጫ፤



አገራችን ኢትዮጵያ በወያኔ ኢህአዴግ ኢ- ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ስር ከምትገባ ሩብ ክ/ዘመን አልፏል። ይህ ፀረ ህዝብ ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ለ25 ዓመታት በሙሉ የአገርንና የህዝብን ጉዳይ ወደኋላ ትቶ የእድሜ ስልጣኑን በሚያመቻችለት ልቅ በሆኑ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባሮች ተሰማርቶ ቆይቷል።

በእነዚህ ባስቆጠራቸው የስልጣን ዘመኑ የህዝባችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተገፎ፤ የህግ የበላይነት ተረግጦ፤ ህዝብ በአምባገነኖች ህግ እየተዳደረ መራራ ስቃይ እንዲያልፍ ተፈርዶበት ቆይቷል። ይህ ጭቆና የወለደው ሰብዓዊነቱ የተገፈፈ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ይህንን ፀረ ዴሞክራሲ ስርዓት በመቃወም ድምፁን እያሰማ ይገኛል።

ስርዓቱ ግን የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ሰምቶ ተገቢ የሆነ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ በጠመንጃ አፈሙዝ ለማንበርከክ ሲሞክር ታይቷል። ይህንንና ሌሎችን የኢህአዴግ የ10 ዓመት ጉዞ ፀረ ህዝብ ተግባሮች በመገምገም፣ በኢህአዴግ አረመኔያዊ ቡድን ስር ሆኖ በሰላማዊ ትግል መልክ በምርጫ ተወዳድሮ ጨቋኙን የኢህአዴግ ስርዓት አስወግዶ ህዝባዊ ስልጣን ለመያዝና ትክክለኛ ፍትህ፤ ዴሞክራሲና ሰላምን ማንገስ አይቻልም የሚል መደምደሚያ ለመውሰድ አስቸጋሪ አልነበረም።

እነሆ ደግሞ ህዝባችን የትግራይ ህዝብ፣ ወያኔ ኢህአዴግ በጠመንጃ ሃይል እንጂ በሰላማዊ መንገድ ስልጣኑን ለህዝብ ሊያስረክብ እንደማይችል ከ15 ዓመት በፊት ሊያረጋግጥ በመቻሉ የስርዓቱን ባህርያት በሚገባ ገምግሞ፣ ወያኔ ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል ብቻ ነው ሊወገድ የሚችል የሚል አቋም ይዞ በስርዓቱ ላይ የትጥቅ ትግል ለመጀመር ተገዷል።

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፦ ወያኔ ኢህአዴግ ከአመሰራረቱ  ፀረ ዴሞክራሲ ስለሆነ ከመጀመሪያው ጀምራችሁ እየታቀወማችሁ መጥታችኋል፥ ስርዓቱም በህርያቱ እንደሚገልፀው በሰላማዊ መንገድ መብቱን ለጠየቀ ህዝብ እየጨፈጨፈውና እየገደለው መጥቷል። ወያኔ እስካሁን በሁሉም የአገራችን ማዕዘን ያጠፋውን የንፁሃን ዜጎቻችን ህይወት ህዝባችን በግልፅ ታውቀዋለህ።

ይሁን እንጂ ይህ ስርዓት በእሱ ላይ የሚነሱትን ህዝባዊ ተቃውሞዎች የጥይት ግብረ መልስ ስለሰጣቸው፤ አቁሞ ሊያቆመው አልቻለም። የዚህ ሁሉ ውጤት ደግሞ ወደ ሌላ ሳንሄድ በዚህ አመት ብቻ እየተካሄዱ ያሉት ሰልፎችን ማየት እንችላለን።

ከ8 ወራት በፊት በኦሮሞ ህዝብ ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተነሳ የተዳፈነ እሳት በጥቂቶች ተነስቶ፣ ተቃውሞውን ለማጥፋት በስርዓቱ የተወሰደ የአፀፋ እርምጃና እየተሰጠ በነበረ ማስፈራሪያና መግለጫ ሊታገት አልቻለም። እንዲያውም በጠነከረ መልኩ ተቀጣጥሎ በሁሉም አካባቢዎች በመዳረስ የ400 ንፁሃን ዜጎች ህይወት በስርዓቱ ሲቀጠፍ፣ ከ10 ሺህ በላይ ወገኖች ደግሞ እንደታሰሩ የሚታወቅ ነው።
አሁንም ፍትህ፤ ሰላምና ዴሞክራሲ ፈላጊ የሆነው ጭቁን ህዝብ ይህ አረመኔያዊ ስርዓት በሚያወርደው ግርፋት፤ ግድያና እስራት ሳይንበረከክ ትግሉን እያቀጣጠለ የልጆቹን ህይወት በየቀኑ በስርዓቱ የፀጥታ ሃይሎች አውራ ጎዳና ላይ እየገበረ ይገኛል። ሰሞኑን ደግሞ በአብዛኛው የአገራችን ክልሎች በተለይ ደግሞ በአማራ ክልል ተቃውሞው ሊቀጣጠል ችሏል።

የተከበርህ ህዝባችን፦  ይህ ስርዓት በተፈጥሮው ፀረ ህዝብ ስለሆነ በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ባለው ጠንካራ ህዝባዊ ተቃውሞ የንፁሃን ዜጎቻችንን ህይወት በመሃል መንገድ በጥይት ከመቅዘፍ ወደኋላ አላለም፥ የበርካታ ዜጎቻችንን ህይወት አሳልፏል። በዚህ አጋጣሚ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) የተሰማውን መራራ ሃዘን ይገልፃል።

ድርጅታችን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ይህንን መግለጫ ሲሰጥ ከሩብ ክ/ ዘመን በላይ ያህል በወያኔ ኢህአዴግ  አፈናና ሙስና በነፃነት ጥማት የተነሳ ህዝብ እያሳየው ላለው ማዕበላዊ ትግል ከጎኑ እንደሚቆም እየገለፀ።
የሚካሄደው ተቃውሞ አንድ ጊዜ በኦሮሞ፤ በትግራይ፤ አንዴ ደግሞ በአማራ ከሚሆን በአንድ ቦታ ለከፍተኛ ተቃውሞ ሁላችንም ልንከተለውና አንድ መሰረታዊ ለውጥ እስከሚመጣ፣ አንዱ ተቃዋሚ አንዱ ታዛቢ ሳይሆን የጋራ ጠላት፣ የጋራ ክንድ ሊያርፍበትና ፈጣን ለውጥና ድል የሚያመጣ ህብረት አስፈላጊ መሆኑን ድርጅታችን ትህዴን በዚህ አጋጣሚ መልእክቱን ያስተላልፋል።
                                               ድል ለጭቁኖች!!
የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን)
                    ነሐሴ 2008 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment