Monday, April 3, 2017

የኢህአዴግ ጥናትና ምርምር በስልጣን ለመቀጠል የሚደረግ ጣረ-ሞት ነው!!




    አንድ አገርና ህዝብን ወክሎ አስተዳድራለሁ የሚል ስርዓት እየተከተለው ያለው መመሪያም ይሁን ፖሊሲ መለኪያው የዜጎችን ሁለንተናዊ እድገትና ተጠቃሚነት በማሳደግ፣ ሰላም፤ ፍትህ፤ ዴሞክራሲ፤ ልማትና መልካም አስተዳደር በተግባር ሲያረጋግጥ ነው።
   እነዚህ ወደፊት እንዳይራመዱ የሚያደናቅፉ እንከኖች ሲያጋጥሙ ደግሞ ከስረ መሰረታቸው ነቅሎ ለመጣል ጥናቶችን በማካሄድ ድክመቶቹን በተገቢው መንገድ በማስተካከል በአገሪቱ በዋናነት ደግሞ በህዝቡ ዘንድ ተጨባጭ የተግባር ለውጥ ማምጣት አለበት።  
   ይህንን መንገድ ስቶ በራሱ አለም ለመኖር ላይና ታች የሚል ስርዓት ከሆነ ግን፣ ፖሊሲው የውድቀት፤የሁከት፤ የኋላቀርነትና የድህነት መንገድ ከመሆን ባለፈ የሚያረጋግጠው ሰላም፤ ልማት፤ ዴሞክራሲም ይሁን መልካም አስተዳደር የለም።
    ይህንን ካልን አገራችንን እና ህዝባችንን ለአደጋ አጋልጦ ያለው ውጤት አልባ የሆነ የወያኔ ኢህአዴግ ፖሊሲ ለማየት ስለፈለግን ነው። ይህ የጥቂቶች ቡድን  ስርዓት በየጊዜው እየተከተለው የመጣውና ያለው አውዳሚ ፖሊሲው የአገራችንን ህዝቦች አንድነት በጣጥሶ ለይምሰል የአንድነት መዝሙር እያሰማ እልም ወዳለ የድህነትና አደጋ ገደል እያሽቆለቆለ፣ በጣፋጭ የተስፋ ቃላት አጅቦ እድገት እያለ የራሱን ገነት የፈጠረ ነው።
    ይህ እየተከተለው የመጣውና ያለው አውዳሚ ፖሊሲውና አስተዳደሩ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በየወቅቱ አስተካክል እያለ እየመከረው የመጣ ቢሆንም እንኳ፣ የህዝቡን ምክርና ማስተካከያ በቀናነት አይን ተመልክቶ በጊዜው ከአደጋና ጥፋት የሚያድን መፍትሄ ለማመቻቸት ህሊናው አልፈቀደለትም።
   ህሊናው ከህዝብ ርቆ በግላዊ ህይወቱና በግላዊ ኑሮው የተዘፈቀ አካል ደግሞ ለህዝብና ለሃገር በዘላቂነት የሚዋስ ተግባር ይስራል ተብሎ አይጠበቅም። ስለሆነም ይህ ፀረ ህዝብ ስርዓት ያለውን የስልጣን ስስት ለማርካት ሲል መቆያ ይሆኑኛል ያላቸውን የተለያዩ ስልቶች ለመፈብረክ ግድ ሆኖበታል።
   ለዚህ ከወገኑ በየጊዜው ሲቀርብለት የቆየውን ምክር ጀሮ ዳባ ልበስ በማለት አራጊ ፈጣሪ ሆኖ ወደ ምን ደረጃ አድርሶታል? እጣው ምን እየጠበቀው እንዳለ በሚገባ ስለሚያውቅ፣ ለዚህ ሁኔታ የተለያዩ መምሪያዎችንና አዋጆችን እያወጣ ነጋ ጠባ በመገለባበጥ አስተካክላለሁ ቢልም እንኳን፣ የመጀመሪያው አስቀድሞ ህዝብና ሃገርን ለአደጋ እያጋለጠ የኋለኛው ይሻላል የሚባልበት መንገድ የለም።
  የዚህ ምሳሌ ባለፈው አመት የፌደራል የስራ አስፈፃሚ አካል በገለጠው መሰረት በአገሪቱ የተፈጠረው ስህተትና አደጋ ተጠያቂው የላይኛው አካል እንደሆነ በመግለፅ ከዚህ ጋር አያይዞ ደግሞ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በተደረገው ጥናት በሚል ስለ መልካም አስተዳደር መድረኮች አገራዊ አጀንዳ በማድረግ የችግሮች ባለቤት የሆኑትን አስወግዶ ታምር የሆነ ለውጥ እንደሚፈጠር ተነግሮ ነበር።
   ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ተደብቀው የቆዩ መሰረታዊ ጥያቄዎች ፈንድተው ወደ አደባባይ በመውጣት ማደናገር ይበቃል፤ ጭቆና ይበቃል፤ ሲላቸው ታይቷል። በዚህ ሁኔታ የተፈጠረ እልቂትና ውድመት ደግሞ ቤት ይቁጠረው የሚያሰኝ ነው።
   በአሁኑ ወቅት ደግሞ የተናገሩትን ረስተው እንደገና በአዲስ፣ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የተጠና ተብሎ ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች በሚዲያ ሲገለፁ ይታያል። ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ያለምንም ለውጥ የቀጠለ ስርዓት ዛሬ ላይ ደርሶ የለውጥ መንኮራኩር ሊያመጥቅ አይችልም።
በአገሪቱ አንጃበው ያሉት ሁለንተናዊ ችግሮች፤ የህዝብ ወሳኝነትና የህግ የበላይነት በተግባር ነጋ ጠባ ከሚቀያየር መምሪያ በስተቀር መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም።
  

No comments:

Post a Comment