Thursday, May 25, 2017

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ደርሶ ከነበረው አደጋ የተረፉ ሰዎች ቃል የተገባላቸው የገንዘብና መጠለያ ቤት ድጋፍ እስካሁን ድረስ እንዳልተሰጣቸው አስታወቁ።



ከ130 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው አደጋ ተከትሎ በርካታ መንግስታዊ ተቋማት የግል ባለሃብቶች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ከአደጋው የተረፉ ሰዎች መልሶ ለማቋቋም ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ለግሰው እንደነበር በወቅቱ ቢገለጽም፣ የተጎጂ ቤተሰቦች በባንክ አካውንታቸው ውስጥ አንዳችም የገባ ገንዘብ አለመኖሩን ተናግረዋል። ገንዘቡ እንደገባላቸው የባንክ አካውንት ክፈቱ ተብለው አካውንት መክፈታቸውንም አስታውሰዋል።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት እነዚሁ ተጎጂዎች የተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው የገለጹ ሲሆን፣ በቀን ሶስት ጊዜ ሲቀርብላቸው የነበረ የምግብ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ተቀንሶ በየዕለቱ ከ9 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት አንድ ላይ እንደሚመጣላቸው ተናግረዋል።
በአደጋው ስድስት ቤተሰቦቻቸውን እንዳጡና በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለስምንት አመታት ያህል እንደኖሩ የተናገሩት አቶ ተመስገን መኮንን የተባሉ ተጎጂ ቃል የተገባላቸውን ቦታ ምትክ እንዳላገኙ አስረድተዋል። ምግብ እንኳን የሚያገኙት ከጓደኞቻቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment