Sunday, June 11, 2017

በትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ ትህዴንና በአርበኞች ግንቦት 7 መካከል በትብብር ለመስራት የተደረገውን ስምምነት አስመልክቶ የተሰጠ የጋራ መግለጫ፦



    የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት በህዝብ ልጆች መስዋእትነት ተረማምዶ ስልጣን ከተቆናጠጠ ጊዜ አንስቶ በትግሉ ወቅት ለህዝብ የገባለትን ቃል ኪዳኖች ወደ ጎን በመግፋት በግል ጉዳዮቹ ብቻ በማተኮር ባለፉት 26 ዓመታት የአገዛዙ ወቅት ኢ-ዴሞክራስያዊ  አካሄዱ በፈጠረው ችግር በህዝባችንና በአገራችን ከፍተኛ ግፍና በደል ሲፈፅም ቆይቷል አሁንም  በመፈፀም ላይ ነው።
  ፀረ ህዝብ ስርዓት ለ26 አመታት በሃይል አፍኗቸው የቆዩ የህዝብ ጥያቄዎች ፈንድተው በአሁኑ ወቅት ህዝባዊ ማእበል ከአቅሙ በላይ ሆኖበት የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ህዝባችን ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የእለት ጉርሱን እንዳያገኝና ለችግሩ መፍትሔ እንዳያፋላልግ አሳስሮ በመያዝ የስልጣን እድሜውን የሚያራዝምለት መስሎት የጣረ ሞት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
  ተጨባጩን የአገራችንና የአካባቢያችንን ሁኔታ  በጥልቀት በመግምገምና ተባብሮና ተቀራርቦ መስራት አማራጭ የሌለው ወቅታዊ ሁኔታ መሆኑን በማመን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ ትህዴንና የአርበኞች ግንቦት 7 በፖለቲካዊው፤ በወታደራዊው እንዲሁም በማህበራዊውና በዲፕሎማስያዊው መስክ ተቀራርበውና ሁለንትናዊ አቅማቸውን አስተባብረው በተግባር ለመስራት ተስማምተዋል።
  በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምትገኝ ጭቁን የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፣ በማካሄድ ላይ የምትገኘው ሁለንትናዊ ትግል ያለንን አድናቆት እየገለፅን በአገራችን ላይ ያለውን አፈናና ጭቆና እንዲያበቃ በሁለቱም ድርጅቶች የተወሰደውን አብሮ የመስራት ተነሳሽነት ለመደገፍ የምታደርገውን ሁለንትናዊ እገዛ እንድታሳድግ ጥርያችን እናቅርባለን።
የተከበራችሁ የአገራችን ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ በአሁኑ ወቅት በህዝባችን ትክሻ ላይ ተጭኖ የሚገኘው የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት አገዛዝ እስካሁን በስልጣን ላይ ሊቆይ የቻለው ስርዓቱ አቅምና ህዝባዊ ድጋፍ ኑሮት ሳይሆን ሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ተባብረው ያለመስራታቸው ያገኘው እድል መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው።
ስለሆነም አሁንም አማራጩ ተባብሮና ተቀራርቦ መስራት መሆኑን በማመን በሁለቱም ድርጅቶች የተወሰደውን ተነሳሽነት በመከተል ልዩነታችን በማጥበብና የህዝባችንን ጥቅም በማስቀደም  እንድንሰራና  ህዝባዊ ሃላፍነታችን እንድንወጣ ጥርያችንን እናቅርባለን።
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የስርዓቱ አገልጋዮች የሆናችሁ ካድሬዎች  የፀጥታ አካላት የመከላከያ ሰራዊት እና ሌሎችም ቋሚ ህዝብ እንጂ ቋሚ መንግስት እንደማይኖር ከአሁኑ በመረዳት በህዝባችሁ ላይ እምትፈፅሙት ግፍና በደል ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ተረድታችሁ ከህዝባችሁ ጎን በመሰለፍ የህዝብ ወገናዊነታችሁን እንድታራጋግጡ ትህዴንና አርበኞች ግንቦት 7 ጥርያቸውን ያስተላልፋሉ።
               ድል ለጭቁኖች!!  አንድነት ሃይል ነው!!
               ትህዴንና አርበኞች ግንቦት 7
                          ግንቦት    2009 ዓ.ም 

No comments:

Post a Comment