Tuesday, April 3, 2018

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ሥር ለሰደደው የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡ ይገባቸዋል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቀረበ።



 አዲሱ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አብይ አህመድ በመላው አገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውንና ሥር የሰደደውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ለመፍታት ከሁሉም ነገሮች ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል።
  አገሪቷ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት የተለያዩ የዜጎችን ነጻነት የሚገድቡ ሕጎች ተግባራዊ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩለት፣ ነጻነት እንዲሰፍን በሚጠይቅበት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ወደ ስልጣን መጥተዋል። አስቸኳይ አዋጁ እንደታወጀ እጅግ አስደንጋጭ ክስተቶች በአገሪቱ ተከስተዋል። የካቲት 24 ቀን 2010 ዓም በደቡባዊ ኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ በአገዛዙ ታጣቂዎች በተወሰደ ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ 12 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለው በርካቶች ቁስለኛ የሆኑበት ለአብነት ማሳይ ተደርጎ ይወሰዳል በማለት አምነሰቲ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ጠቃቅሷል።
 በያዝነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ የተለቀቁ 12 ታዋቂ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ተመልሰው እንዲታሰሩ ተደርገዋል። በተመሳሳይ ባህርዳር ከተማ 19 ሙሁራንም ታስረዋል። ”የሰላማዊ ዜጎች ግድያ፣ የፖለቲካ እስረኞችን ፈቶ ዳግም እንዲታሰሩ ማድረጉ አገዛዙ የገባውን የለውጥ ተሃድሶ ቃልኪዳን አጠያያቂ ያደርገዋል። የጠቅላይ ሚንስትሩ ሹመት በፓርላማው ሲጸድቅ ሁሉንም እስረኞች ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች በመፍታት፣ ሁሉንም አፋኝ ሕጎችን ማንሳት አለበት። ”ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሃፊ ሳሊል ሼቲ አክለው ተናግረዋል።

 

No comments:

Post a Comment