Monday, November 12, 2012

በመቐለ ከተማ የሚገኙ ነጋዴዎች መንግስት መክፈል ከሚገባን በላይና አቅማችንን ያላገናዘበ ግብር በመጫን እንድንከፍል እያስገደደን ነው ሲሉ ያማርራሉ ።





ኗሪነቷቸው በመቐለ ከተማ የሆኑ በርካታ ነጋዴዎች እንደሚሉት መንግስት በአሁኑ ግዜ እየተከተለው ያለ የግብር አከፋፈል አሰራር በጥናት ያልተደገፈ ፣ ሚዛናዊነት የጎደለውና በአድልዎ የተሞላ በመሆኑ በሞያው በሃላፊነት የተሰማሩ ካድሬዎች በማን አለብኝነት ያሻቸውን ያደርጋሉ ። አንዳንዶችን መክፈል ከሚገባቸው በታች እንዲከፍሉ ሲደረግ አብዛኛዎቹ ነጋዴዎች ግን ገቢያቸውንና ወጭያቸውን በአግባቡ ሳይመዛዘን መክፈል ከሚገባቸውና ከአቅማቸው በላይ እንዲከፍሉ ተጠይቀው መክፈል ስላልቻሉ የንግድ ድርጅቶቻቸው የታሸጉቧቸው ሲሆን የተወሰኑት ነጋዴዎች ተበድረውም ቢሆን የተጠየቁትን ግብር እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ከቦታው የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
በዚህ መሰረት በከተማዋ ከሚገኙት በርካታ ትላልቅ ነጋዴዎች መካከል በመሸሻና ወድመቹን በሚል የንግድ ስያሜ ጥላ ስር በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ማከፋፈያ ፣ የዘመናዊ አልባሳት ማከፋፈያና ዘመናዊ ፎቶ ቤት ባለ ንብረት የሆኑት አንድ ነጋዴ ለፎቶ ቤቱ ብቻ 2.3 ሚልዮን ብር ግብር እንዲከፍሉ በመንግስት ተጠይቀው ግለሰቡ የተጠየቁትን ግብር እጅግ የተጋነነና አመቱን ሙሉ ሰርተው ከሚያገኙት ገቢ በላይ በመሆኑ ዳግመ-ግምት እንዲደረግላቸው ጠይቀው ሰሚ ስላላገኙ ድርጅታቸውን ጣጥለው ተሰወረዋል። ድርጅታቸውም እስካሁን ድረስ እንደታሸገ መሆኑ ለማወቅ ተችለዋል።
በተመሳሳይ በከተማዋ ኗሪ የሆኑ አንዲት እናት የንግድ ፈቃድ መነሻ ካፒታል 3ሺ ብር ተመዝግቦ እያለ 6ሺ ብር ግብር እንዲከፍሉ ተጠይቀው ከአቅማቸው በላይ ሆኖ መክፈል ስላልቻሉ ክስ ተመስርቶባቸው  ፍርድ ቤት በመመላለስ ላይ ይገኛሉ ። እንደዚሁም የቀበሌ 18 ኗሪ የሆኑ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ሌላ እናት በአከራይና ተከራይ የተመዘገቡ ሲሆን 8ሺ ብር እንዲከፍሉ በተጠየቁበት ግዜ እየሆነ ያለው ሁሉ ህጋዊነት የተላበሰ ዝርፊያ ነው ብለው በመናገራቸው መታሰራቸውንና የተጠየቁትንም ግብር ለመክፈል መገደዳቸውን ቷውቋል።
በመጨረሻም እንዲህ አይነቱ ወጥነት የሌለው የግብር አከፋፈል ፖለቲካዊ ይዘት ያለው በመሆኑ የኢህአዴግ ደጋፊዎች አይደሉም ተብለው በድርጅቱ ካድሬዎች የታመነባቸው ነጋዴዎችን በማስፈራራት ፣ በማሸማቀቅና በማሰር ከንግዱ ዓለም እንዲወጡ ለማድረግ እንደ አንድ ግብ ተይዞ እየተሰራበት ነው ሲል የደረሰን ዘገባ ጨምሮ ያስረዳል ።
ከዚህ በፊት በአ/አበባ ፣ በናዝሬት ፣ በወረታና በመሳሰሉት ከተሞች የታየውን የግብር አወሳስን ችግር አስመልክተን መዘገባችን የሚታወስ ነው።