ኢትዮጵያዊያን የእስልምና እምነት ተከታዮች የእምነት ነጻነት መከበር ህገ-መንግስታዊ መብታቸው በመሆኑ መንግስት
በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ማስገባት ያቁም? ፤ መሪዎቼን እራሴው ልምረጥ? ፤
የአውልያ ኮሌጅ በነጻ ቦርድ ይመራ? በማለት ያስነሱዋቸውን ጥያቄዎች እስካሁን ድረስ ምላሽ አላገኙም።
የኢህአዴግ ስርዓት ህገ-መንግስቱን በማከበር ለሚነሱ መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎች
በአግባቡ ምላሽ መስጠት ሲገባው የሙስሊሙን ማህበረሰብ የማይወክል የተለያዩ ስሞችን በመለጠፍ ጾታና እድሜ ሳይለይ በእምነቱ ተከታዮች
ላይ በደል በመፈጸም ላይ ነው።
ለዚህም ነው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ድምጻችን ይሰማ ? ጥያቅያችን ይመለስልን በማለት ከሁለት ዓመታት በፊት
የጀመረውን ተቋውሞ አጠናክሮ በመላ ሃገሪቱ እየቀጠለበት ያለው።
ሁለት ዓመት ለመድፈን ጥቂት ወራት የቀረው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቋውሞ ትክክለኛና የማያሻማ ቢሆንም የኢህአዴግ
ስርዓት ግን የእምነቱ ተከታዮች ለሃይማኖታቸው በመቆማቸው ብቻ አክራሪ ሃይሎች የሚል ስም እየለጠፈ የእንቅስቃሴውን አመራሮችንና
በርካታ የሃይማኖቱ ተከታዮችን በየ እስር ቤቱ በማጎር እያሰቃያቸው ይገኛል።
ኢህአዴግ ገና ሲጀመር ለከሸፈበት ተግባሩ የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮችንና የዓለም ማህበረሰብ ድጋፍ ለማግኘት
ሲል በየእስር ቤቱ ያጎራቸውን የሙስሊሙ ማህበረሰብ እንቅስቃሴ አመራሮችን በማሰቃየት ፤ ዓላማቸው እስላማዊ መንግስትን መመስረት
ነው በማለት እንዲናገሩ በማድረግና ጅሃዳዊ ሃረካት የተሰኘውን ድራማ መንግስት በሚቆጣጠረው ሚድያ ደጋግሞ በማሰተጋባት ህዝቡን ለማደናገር
መሞከሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
አሁንም ቢሆን እኩይ ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል መብቱ ለጠየቀው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሌሎች ወንድሞቹ
ለመነጠልና በጠላትነት እንዲታዩ ለማድረግ ሲል መብታቸው እንዲከበርላቸው በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ሲያቀርቡ በነበሩ የሙስሊሙ ማህበረሰብ
መካከል የራሱ ሰዎችን በማስገባትና ባንዴራ በማቀጠል ሙስሊሙ ባንዴራ እንዳቃጠለ አስመስሎ በማቅረብ የኢህአዴግን ስርዓት ተንኮል
ለማይገባቸው ለማታለል እየሞከረ ነው።
ከዚህም አልፎ ከመጀመሪያ ጀምሮ ያለማቋረጥ በሁሉም በሃገራችን የሚገኙ መስጊዶች እየተካሄደ ያለው ጠንካራ
ተቃውሞ ለማፈን በእልስምና እምነት ተከታዮች ላይ እርምጃ እየወሰደ መቆየቱ የሚታወቅ ሆኖ በአሁኑ ደግሞ በከፋ መልኩ በዒድ-አልፈጥር
ለፈጣሪያቸው ጸሎት አድርሰው በሰላም ወደየቤታቸው ሲመለሱ በነበሩ ዜጎች ላይ የተወሰደው የሃይል እርምጃ የአንድ ፋሽሽታዊ ስርዓት
መገለጫ ነው።
በተለያዩ የሃገሪቱ ከተማዎች ብዙ ዜጎች ህጻናት ሳይቀሩ ምንም ጥፋት ሳይኖራቸው በመጨፍጨፍ በይ እስርቤቱ
በማጎር እያሰቃያቸው ይገኛል።
ስለዚህ ጸረ-ህዝቡ ስርዓት መብታችሁን ለምን ጠየቃችሁ በማለት እኛን በማፈን እራሱን በስልጣን ላይ ለመቆየት
እያደረገው ያለ ከንቱ ሙከራ ቅዠት ሆኖ እንዲቀር ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የሙስሊሙን ህዝብረተሰብ ያነሳውን የሃይማኖት መብት ይከበር
ጥያቄ በመደገፍ በአንድ ድምጽ ከሙስሊሙ ጎን ሊሰለፍ ይገባል።
የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) የኢህአዴግ ስርዓት በህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩትን የሃይማኖት
ነጻነት በመጣስ በሙስሊሙ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ ያወግዛል-ይታገለዋል።
ትህዴን ሃይማኖታዊ መብቶች ይከበሩ በሚል በሙስሊሙ ህዝብረተሰብ እየተካሄደ ያለውን ተቋውሞ ከልብ በመደገፍ
ከጎናቸው እንደሚቆም ዳግም ያረጋግጣል።
ድል ለጭቁኖች
ትህዴን ነሃሴ 2005 ዓ/ም