Tuesday, September 10, 2013

የ2006 ዓ/ም አዲሱ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ት.ህ.ዴ.ን) የተሰጠ ደርጅታዊ መግለጫ

ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ለጀግኖች የትህዴን ታጋዮች፤ ለድርጅቱ አባላት፤ ለትግሉ ደጋፊዎችና ለተቃዋሚ ድርጅቶች ሁሉ እንኳን ለ2006 ዓ/ም አዲስ ዓመት አደረሰን አደረሳችሁ።
እንደሚታወቀው አምባገነኑ የኢህአዴግ ስርዓት በሚከተለው ኢ-ዲሞክራሲያዊና ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱ ተረግጦ በከፋ ጭቆና ስር መማቀቅ ከጀመረ 22 ዓመታት ተቆጥሯል።
አምባገነኑ የኢህአዴግ ስርዓት ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ይሁንታ ውጭ ስልጣን ከጨበጠበት ጊዜ ጀምሮ የሃገሪቱ ዜጋ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮ በሃገሩ ተንቀሳቅሶ ሰርቶ ለመኖር የሚያስችለው እድል ተነፍጎት በገዛ አገሩ በከባድ ችግር ላይ ይገኛል።
ዜጎች በሃገሪቱ ውስጥ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩና በመረጡት አከባቢ እንዳይኖሩ መከልከላቸው እንዳይበቃ ጥረው ግረው ያፈርቱን ሃብት እየተነጠቁ እንደ ባእድ (ሁለተኛ ዜጋ) ተቆጥረው ከቀያቸው እንዲፈናቀሉና እንዲባረሩ ተደርጓል።
የኢህአዴግ አመራሮች በኢትዮጵያ ህዝብ ስም እየነገዱ ስልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም ኪሳቸውን ሲያደልቡና የስልጣን እድሚያቸውን ያራዝምልናል የሚሉትን አዋጅ በማውጣት የህዝቡን መብት በመጨፍለቅና ህዝቡን ጠፍሮ በመያዝ በሃገሪቱ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ በማደረግ ሲሰሩ ቆይተዋል።
አምባገነኑ ስርዓት እየተከተለው ባለ አፋኝ አካሄድ እድሜና ጾታ ሳይለይ በርካታ ንጹሃን ወገኖቻችንን አፍኖ በመውሰድ በየእስር ቤቱ ቷጉረው ሲማቁቁና አድራሻቸው ሳይታወቅ ድብዛቸው እንዲጠፋ የተደረገ ዜጎችን ስናይና ስንሰማ የኢህአዴግ ስርዓት ምን ያህል ለሃገርም ሆነ ለህዝብ የማቆረቆር ስርዓት መሆኑን የሚያረጋግጥልን ሃቅ ነው።
ዜጎች ተምረው ለቁም ነገር በቅተው ሳይማር ያስተማራቸውን ህዝብና አገራቸውን እንዲያገለግሉ ማድረግ ሲገባ ጸረ-ህዝብ ስርዓት በሚከተለው ብልሹ ፖሊሲ ምክንያት ወደ ስደት ሲያመሩና ለስቃይና ለሞት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል ብቻ ሳይሆን የዓለም መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ዓመታት ተቆጥሯል።
ስለሆነም ጸረ-ዴሞክራሲውን ስርዓት በመቃወም በሁሉም አቅጣጫ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ትግል ፍትሃዊ ነው፥ ምክንያቱን ሁሉ ጊዜ ጭቆና ካለ ከጭቆና ነጻ ለመውጣት ብቸኛው መንገድ መታገልን የሚጠይቅ ነውና፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ የተነጠቀው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባመቸው መንገድ ተደርጅቶ ሃይሉን አጠናክሮ እየታገለ ያለው የተነጠቀውን መብቱንና ነጻነቱን ለማረጋገጥ ሲል ነው።
የኢህአዴግን ስርዓት በመቃወም በመላ ሃገሪቱ በየአቅጣጫው እየተደረገ ያለው ትግል አንድ አካል የሆነው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ከተመሰረተበት እለት ጀምሮ ለዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ ሁሉም ዓይነት መስዋእትነት እየከፈለ መጥቷል። እየከፈልም ነው።
ክቡር የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ!
ባለፉት 22 ዓመታት አምባገነኑ የኢህአዴግ ስርዓት እኔ በምልህ ብቻ ታዘህና አሜን ብለህ ባለመገዛትህ ምክንያት በላይህ ላይ የደረሰ ግፍና ጭቆና በተለይም ዴሞክራሲያዊ መብትህን ለማርጋገጥ እያካሄድከው ያለውን ትግል እንደ ወንጀል ተቆጥሮ አሸባሪ፤ ጸረ-ልማት፤ ጸረ-ሰላም …ወዘተ የሚሉ ስሞች እየተሰጡህ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል እየተፈጸመብህ ይገኛል።
በውድ ልጆችህ ደምና መስዋእትነት ስልጣን የጨበጠው የኢህአዴግ ስርዓት ካለፉት ስርዓቶች በከፋ መልኩ በሚያራምደው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ምክንያት ኑሮህ ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ በመሄዱ ኮትኩተህ ያሳደካቸውና ያስተማርካቸው ልጆችህ የኢህአዴግ ስርዓት በፈጠራቸው ሰብኣዊነት የማይሰማቸው አረመኔ ደላሎች የህልም እንጀራ እየመገቡ በማታለል በአስር ሽዎች የሚቆጠር ብር እያስከፈሉ ወደ ባእድ አገር እንዲሰደዱ በማድረግ ልጆችህ ለስቃይ፤ ውርደትና ሞት መዳረጋቸው እንዳይበቃ አካላቸው ተቆራርጦ ሲሸጥ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ተግባር ነው።
ባለፉት 22 ዓመታት ባንተና በሃገሪቱ ላይ የደረሰው በደልና ግፍ እንዲያበቃ አምባገነኑ የኢህአዴግ ስርዓት ተወግዶ በምትኩ የህዝብ ይሁንታ ያገኘ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲተከል ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ በቶች እንዲከበሩ ህዝቡ ያለ ምንም ልዩነት በልማት እንዲሳተፍና የበለጸገች አገር እንድትኖረን እየከፈልከው ያለ መስዋእትነትን ትህዴን ያደንቃል ከልብ ይደግፋልም፥ መደገፍ ብቻ ሳይሆን አምባገነኑን ስርዓት ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሃገርንና ህዝብን የሚያኮራ መስዋእትነት እየከፈለ መጥተዋል፥ በመክፈል ላይም ይገኛል።
ትህዴን አሁንም ቢሆን እንደወትሮው በስልጣን ላይ ያለው አምባገነኑ ስርዓት ተወግዶ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ያረጋግጣል።
ለኢትዮጵያዊያን የተቃዋሚ ደርጅቶች
በተለያየ መልኩ በየአጣጫው የኢህአዴግን ስርዓት በመቃወም እየተካሄደ ያለው ትግል የማይናቅ ውጤት በማስመዝገቡ የተነሳ ለኢህአዴግ የራስ ምታት እየሆነ መምጣቱ የሚያጠራጥር አይደለም።
ቢሆንም ግን በየአቅጣጫው በተናጠል በመካሄድ ላይ ያለው ትግል ቅንጅት ይፈልጋል፣ ትህዴን በህብረት በመስራት ላይ የሚታየውን ችግር በተለያዩ አጋጣሚዎች ደጋግሞ አንስቶታል። ምክንያቱም በተናጠል የሚደረግ ማንኛውም ትግል ውጤታማ ስለማይሆንና በተጨባጭም ተባብረን መስራት ባለመቻላችን የሚፈለገው ውጤት ሊመጣ አልቻለም። ስለሆነም በሃገሪቱና በህዝቦችዋ ላይ የተጋረጠውን ችግር በአጭር ጊዜ መፍትሄ የሚያገኘው ውህድ እንቅስቃሴ ሲኖር ብቻ ነው ብሎ ትህዴን ያምናል።
ትህዴን ከሁሉም በኢትዮጵያና ህዝቦችዋ አንድነት የሚያምኑ ሃይሎች አብሮ ለመስራት አሁንም እንደወትሮው ዝግጁ መሆኑን እያርጋገጠ በሃገርም ሆነ ከሃገር ውጭ ለሚገኙ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ለጀግኖች የትህዴን ታጋዮች፤ ለድርጅቱ አባላት፤ ለትግሉ ድጋፊዎችና ለተቃዋሚ ድርጅቶች አዲሱ ዓመት 2006 ዓ/ም የድልና የሰላም ዓመት እንዲሆን በዚሁ አጋጣሚ መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
                                            ድል ለጩቁኖች!
                                                ትህዴን
                                           መስከረም 2006 ዓ/ም