የትግራይ ህዝብ ከአብራኩ የተፈጠሩ የሚወዳቸው ልጆቹ መርቆ ወደ ትግል በመላክ በደርግ ስርአት ላይ ለ17
አመታት ባካሄደው መራራ ትግል ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖች ጋር በመተባበር ከ 65 ሺህ በላይ ሰማእታትና እስከ አንድ መቶሺ የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች በመክፈል ግንቦት 20/
1983 ዓ/ም ለድል እንደበቃ ይታወቃል።
የትግራይ ህዝብ ዋነኛው የትግል አላማ ሰላምና እኩልነት ለማረጋገጥና ከጨቋኙ
ስርአት ተላቆ ከሁሉም ያገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ተፈቃቅሮ የሚኖርባት፤ በህግና በስርአት የሚዳኝላት፤ ፍትህና ሰላም የሰፈነባትና
ህዝቦቿ በራሳቸው ቋንቋ ተጠቅመው ባህላቸውና ልምዳቸውን የሚገልፁበትና አንዲት የሚኮሩባት አዲስትዋ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት
በሚል በወቅቱ የነበረውን እልህ አስጨራሽ የትግል መሰናክል እንደሚያጋጥም አምኖና ተቀብሎ አንድነቱን በማጠናከር ነፍጥ ይዞ እየተዋጋ
ከነበረው ታጋይ በማይተናነስ የሚያስገርም አኩሪ ታሪክ ሰርቶ ለተካሄደው ህዝባዊ ትግል ከታጋዮች እጅ ለእጅ ተያይዞ ወደ ድል አብቅቶታል።
ትናንት የልጆቻቸውን የትግል ፍሬ ብርሃን ነው እየተባለ ሲዘፈንላቸው የነበሩ ወላጆች የልጆቻቸውን መስዋእትነት
ሃገርን ለማዳን ነው ብለው በእምነት ቢቀበሉትም ዛሬ ጠያቂና ደጋፊ ወገን አጥተው፤ አካላቸው ደክሞ ከስራ ውጭ በሆኑበት ግዜ የህወሃት
ማሌሊት ክህደት እያስታወሱ ልጆቼ ቢኖሩ ነሮ እንዲህ ባልሆንኩ በማለት በሃዘን ተውጠው የቀረችው የችግር ሂወት እድሜያቸውን ሲያሳልፉ
ማየት ህሊና ላለው ሰው እጅግ የሚያሳዝን ነው።
የህወሃት ማሌሊት መሪዎች ሰኔ 15 የሰማእታት ቀን ተብላ እንድትከበር መወሰናቸው ለማስመሰልና በሰማእታት
ስም ለማደናገር እንጂ አመለካከታቸውና ብልሹ ስርአታቸው ግልፅ ከማድረግ አልፈው ሌላ ትርጉም ሊኖረው እንደማይችል ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ
ህዝብ በተለይ ደግሞ ለትግራይ ህዝብም የተሰወረ አይደለም፣ ምክንያቱም በፈፀመው ገድልና ባስፈፀመው ታሪክ ተገቢ ክብር መሰጠት ሲገባው
ወላጆቹንና ልጆቹን በህወሃት ማሌሊት አመራሮች ተክደው መስዋእትነታቸው ከንቱ ሆኖ ስለቀረ፣፣
ግላዊ ጥቅምና ስልጣንን መነሻ ባደረገው በቡድን ተከፋፍሎ የሚገኘው የህወሃት ድርጅት የአስር ሺዎች ሰማእታት፤የመቶ
ሺዎች የጦርነት አካል ጉዳተኞችና የታጋይ ቤተሰቦች ሃላፊነቱ በጀርባው ላይ መሆኑን ፍፁም ማየት አልቻለም።
ባሁኑ ግዜ ልጆቻቸው በመስዋእትነት የተለዩባቸው ቤተሰቦች ምንም አይነት እገዛ እየተደረገላቸው አይደለም
ጀግኖቹ የተሰውለትን አላማና በትግሉ ወላፈን ሃብቱና ንብረቱ የወደመበት ጭቁኑ የትግራይ ህዝብ ከድሉ ማግስት ጀምሮ ያገኘው ጥቅም
የለም ብቻ ሳይሆን ህዝቡ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ፍትህ፤ ኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት በሰፊው በመንሰራፋቱ ምክንያት
በመላው ያገራችን ክፍል ትልቅ ቀውስ ተከስቷል።
ዜጎቻችን በስርአቱ ታጣቂ ሃይሎች እየታሰሩና እየተገደሉ ያሉበት ሁኔታ
ላይ ሆነን። የሰማእታትን ቀን ማክበር ፍትሃዊነት እንደማይኖረው፤ የሰማእታትን አደራ በቡድን በተከፋፈለው የህወሃት ማሌሊት አመራር
ክህደት እንደተፈፀመ፤ ጀግኖች የታገሉበትና የህይወት መስዋእትነት ለከፈሉበት ህዝባዊ አላማና መስመር የመለስ ራዕይ እየተባለ ታሪካቸው
ለአንባገነኖች ጥቅም እየዋለ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል።
የህወሃት ማሌሊት አመራሮች ተግባር ላይ በማይውሉት
የተስፋ ቃላቶች በየአመቱ ተሳስተን ነበር፤ ስህተታችንን እናርመዋለን እያሉ የስልጣን እድሜያቸውን ለማራዘም ለ23 አመታት ገደማ
በትግራይ ህዝብ ስም እያደናገሩ ህዝቡ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንደማይሆን በሚጠበቀው 2007 ዓ/ም ላይ እንዲካሄድ እየታሰበ ያለው
አስመሳይ ምርጫ ላይ ስልጣናቸው ለማቆየት በማሰብ በሰማእታት ስም እየነገዱ ለተቃዋሚ ድርጅቶች የሃሰት ውንጀላ በማቅረብ ወደ ፍርድ
ቤት እያቀረቡ፤ በውስጣቸው ምንም አይነት ስምምነት ሳይኖራቸው ምዕራባውያን አገሮችን ለማስደሰትና ፍፁም ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እንዳለ
ለማስመሰል ወድያና ወዲህ ማለታቸው ሆን ብለው ህዝቡንና የአለም ማህበረስቡን
ለማደንገር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
ለማጠቃለል ዴሞክራሲያዊ መብት በታፈነበት፤ ጉቦኝነትና ክህደት በሰፈነበት፤ ነጋዴዎች ከአቅማቸው በላይ ግብር
እንዲከፍሉ በሚገደዱበት፤ እርሶ አደሩ በባለ ሃብቶች ስም ከቀዩውና ከለም መሬቱ እየተፈናቀለ በሚገኝበት፤ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ
የተረጋጋ ሁኔታ በሌለበት፤ በሴት እህቶቻችን ላይ የሚፈፀመው የመብት ጥሰትና ሌሎች ፀረ ህዝብ ድርጊቶች በከፋ መልኩ እየቀጠለ ባለበት
ሁኔታ ላይ ሰኔ 15ን የሰማእታት ቀን ብለው መሰየማቸው በሰማእታት ስም መነገድና የሃገሪቱንና የህዝቡን ክብር ማዋረድ እንጂ የጀግኖቹን
ህያው ታሪክ ለማስጠበቅ ተብሎ እንዳልሆነና በሰማእታት ስም የክህደት መዝሙር ማስተጋባት የካሃድያን ባህሪና ተግባር መሆኑ መታወቅ
ይኖርበታል፣፣
በዚህ አጋጣሚም የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ት.ህ.ዴ.ን/ ጀግኖቹ የወደቁበትንና አሁንም እየተሰውለት
ያለው የህዝብ ዓላማ ዳሩ ላይ ለማድረስና የሰማእታትን አደራ ለማስጠበቅ ዛሬም እንዳለፈው ከህዝቡ ጎን ተሰልፎ መስዋእትነት እየከፈለ
ይገኛል፣፣
ዘለአለማዊ ክብር ለሰማእታት
ድል ለጭቁኖች
______________________________________________