Wednesday, February 18, 2015

የሽሬ ከተማ ነዋሪዎች በመልካም አስተዳድርና በፍትህ እጦት ምክንያት እየተሰቃዩ ስለሆኑ በስርዓቱ ላይ ያላቸውን ጥላቻ እየገለፁ መሆናቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አስረድቷል።



በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሽሬ ከተማ የሚገኙ አስተዳዳሪዎች ህግን በመተው በአድርግልኝ ላድርግልህ ጉቦ ስለተጠመዱ ነዋሪዎችም በፍትህ እጦት ምክንያት እየተሰቃዩ መሆናቸውን የገለፀው መረጃው በሙስና ከተጨማለቁት መካከል የከተማዋ ከንቲባ አቶ አታክልቲ መረሳ መሆኑ ተገልጿል።
መረጃው ጨምሮም የሽሬ ከተማ ከንቲባ  የግል ጥቅሙን ለማሟላት ሲል  በሊዝ የሚታደለውን መሬት ከሃብታሞች ጋር ተመሳጥሮ እንደሸጠውና   የገንዘብ ወጪና ገቢ የሚቆጣጠር ኦዲተር ባለመኖሩ የተነሳ በከተማዋ ከሚገኙት  የመንግስት ቤቶች በኪራይ መልክ   የተሰበሰበውን ገንዘብም ለግል ጥቅሙ እንዳዋለው የገለፀው መረጃው አቶ አታክልቲ መረሳ በህግ እንዲጠየቅና ከሃላፊነቱም እንዲወርድ የከተማዋ ነዋሪ ህዝብ በተደጋጋሚ ጥሪ አሰምቶ ሰሚ አካል እንዳላገኘ ለማወቅ ተችሏል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄ ካቀረቡት የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል አቶ ገብረሚካኤል ሃደራ ሲሆኑ በንግግራቸውም በከተማችን የመልካም አስተዳደርም ይሁን ፍትህ የለም  በተደጋጋሚ መፍትሄ ለማግኘት ብየ ባቀረብኩት አቤቱታ ጉቦ እንድከፍል ስለተጠየቅሁና የመክፈል አቅም ስላልነበረኝ አቤቱታየን እንዳቋርጠው ተገድጃለሁ ሲሉ በስርዓቱ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ጥር 23/2007 ዓም በተደረገው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ መናገራቸው ታውቋል።