Thursday, January 31, 2013

በላዕላይ አድያቦ ወረዳ ስር ሲተዳደር የቆየው የዘላዝለ ጣብያ ኗሪ ህዝብ በአስገደ ጽምብላ ወረዳ ስር ሆኖ እንዲዋቀር ላቀረበው ጥያቄ እስካሁን ድረስ በስርዓቱ የተሰጠ ምላሽ እንደሌለ ከቦታው የደረሰን ዘገባ ያመለክታል፣


በደረሰን ዘገባ መሰረት የዘላዝለ ጣብያ ህዝብ በላዕላይ አድያቦ ስር ሆኖ መተዳደር ያልፈለገበት ዋና ምክንያት በርቀት ሲሆን አስገደ ጽምብላ ግን ቅርበት ስላለው በዚሁ ወረዳ ስር ሆኖ መተዳደርን  ይመርጣል፣  የጣብያው ኗሪ ህዝብ በተወካዮቹ በኩል ለሚመለከታቸው የመስተዳድር አካላት ጉዳዩ አቅርቦ መልስ ባለማግኘቱ ህዝቡ አንድ ላይ በመሆን ወደ ላዕላይ አድያቦ ማእከል ዓዲ-ዳዕሮ ከተማ ድረስ በመሄድ ቁርጡን አሳውቁን በማለት ለወረዳዋ የመስተዳድር አካል ጥያቄውን አቅርቧል፣
በሁኔታው ያልተደሰተ የወረዳዋ የመስተዳድር አካል ከህዝብ ለቀረበለት ጥያቄ በአግባቡ መልስ መስጠት ሲገባው የፖሊስ ሃይል በመላክ የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በሃይል ለማፈንና ህዝቡንም ለመበተን ሙከራ አድርጓል ፣ ነገር ግን ህዝቡ ፖሊሶችን በመቀበል ከናንተ ጋር የሚያገናኘን ምንም ነገር የለም ላቀረብነው ህጋዊ ጥያቄ ከሚመለከተው አካል ህጋዊ ምላሽ ይሰጠን ነው እያልን ያለነው በማለት ከፖሊስ አባላት ሳይጋጭ በስርዓቱ ላይ ያለውን ቅሬታ ገልጸዋል፣
ይህ በእንዲህ እያለ በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ ከልክ ያለፈ ንረት የተማረረው የከተማ ኗሪ ህዝብ ገበያን ማረጋጋትና የህብን ኑሮ ማሻሻል ያልቻለው የኢህአደግ ስርዓት ሃገርንና ህዝብን የማስተዳደር ብቃት አለው ብለን አናምንም በማለት በስርዓቱ እየቀረበ ያለውን የምርጫ ካርድ ውሰዱ ጉትጎታ ውድቅ ማደረጉን ቷውቋል፣