Saturday, January 13, 2018

በህዝብ ስም እየማሉ፥ ኢ-ህዝባዊ ተግባራትን መፈፀም ይቁም!!



አገራችን ኢትዮጵያ በሲኦላዊ አስተዳደር ስር ከምትወድቅ ድፍን 27 ዓመታትን አስቆጥራለች። ይህ የበግ ለምድ ለባሹን ተኩላ ድርጊት የሚፈፅመው ኢ-ህዝባዊና ፀረ ኢትዮጵያ ቡድን በህዝብ ስም እየማለና ራሱን እያወደሰ፣ ህዝብን በማይጨበጡ ተስፋዎች እያደናገረ የሚፈፅማቸውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ተግባሮች ተከትሎ የሚነሱትን ተቃውሞዎች ለማክሸፍ፣ በህዝብ ላይ የሃይል እርምጃ እየፈፀመ መጥቷል። አሁንም እየፈፀመ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የወያኔ ኢህአዴግ አፈናና ረገጣ አንገፍግፎት ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ በቆራጥነት የተነሳውን ማዕበል ለማቀዝቀዝ በለዘብተኝነት፣ ችግሩ የእኛ የአመራሮች ነው፤ አገርንና ህዝብን አደጋ ላይ ጥለናል፣ ይቅርታ እንጠይቃለን፤ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስና ለዴሞክራሲያዊነት ቆርጠን ተነስተናል በሚል የተለመደ የመማፀኛ ቃላት በመደርደር የለውጥ ሃይል መስሎ ለመቅረብ እየሞከረ ይገኛል።
ነገር ግን እነዚህ በወያኔ ኢህአዴግ ቃል እየተገቡ ያሉት ተስፋ ቢስ ንግግሮች ከዚህ በፊትም በስርዓቱ ሲዘመሩ የነበሩ ማደናገሪያዎች እንጂ ይዘውት የመጡት አዲስ አሰራርና ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም፣ የአገሪቱን ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊፈታ የሚችል ፖሊሲ እና እስትራቴጂ አይታይበትም።
በአሁኑ ጊዜ ወያኔ ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹ እያካሄዷቸው የሚገኙት ስብሰባዎችም የሚያሣዩን በድርጅቶች መካከል የተከሰተውን የስልጣን ሽሚያና አንዱ በአንዱ ላይ የሚወስደውን የበላይነት የመቀበልና ያለመቀበል የገቡበትን እሰጥ አገባ እንጂ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ የመፍትሔ አቅጣጫን ማፈላለግ ላይ እንዳልሆነ ከመግለጫውም ይሁን ከየድርጅቶቹ ሊቀመናብርት ልሳን ታዝበናል።
ወያኔ ኢህአዴግ አሁን ያለበት አቋም ስርዓቱ እንደ ስርዓት የሚቀጥልበትም ሆነ አገሪቱን እንደ ሃገር ለመምራት በሚያስችለው አቋም ላይ ሳይሆን እርስ በርሱ በውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ እጦት እየታመሰ ያለበት፤ ከቀደሙት ጊዜያት በከፋ መልኩ ዓይን ባወጡ የሙስናና የብልሹነት አዘቅት ውስጥ የተዘፈቀበት፤ እራሳቸው ያፀደቁትን ህገ መንግስትና የቀረፁትን ፖሊስም እንኳን ማስቀጠል ያልቻሉበት፤የክልል መንግስታት በፌደራሉ መንግስት ስር ተማክለው ላለመሄድ ግብግብ የገጠሙበት፣በአጠቃላይ የስርዓቱ አመራሮች በስርዓት አልበኝነት መንገድ ውስጥ በመጓዝ ህገ ወጥ ተግባራትን እየፈፀሙ አገሪቱንና ህዝቡን ለአደጋ አጋልጠው ያሉበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን ኢህአዴግ ከስህተታችን ተምረናል፤የችግሩ ፈጣሪዎች እኛው ነን ቢልም ችግሩን የፈጠረው እና አገርንና ህዝብን ለማፈራረስ አደጋ ያጋለጠው ፀረ ኢትዮጵያዊ አካል ተለይቶ ተጠያቂ ሲሆን ግን አልታየም። ይህ ደግሞ በስርዓቱ ውስጥ የተጠያቂነት ዴሞክራሲያዊ አሰራር አለመኖሩንና የህግ የበላይነት አለመከበሩን የሚያሳየን በቂ ምስክር ነው።
ስርዓቱ በህግ የበላይነት የሚመራ ቢሆንማ ኖሮ ለእነዚህ ችግሮች መንስኤ ተጣርቶ በህግ አገባብና አሰራር መሰረት ወንጀለኛው ባለስልጣን ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት በቻለ ነበር። ግን ይህ ሲሆን አልታየም። ምክንያቱ ደግሞ ከታችኛው እስከ ላይኛው የቡድኑ አመራሮች በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ተዘፍቀው በመቆየታቸው ጉዳዩን ሸፋፍነው በማለፍ፣ ህዝብን አሁንም ልንበድልህ አንድ እድል ስጠን በሚል የአስመሳይነት አባዜ ውስጥ አልፈውታል።
ነገር ግን ህዝብን እየበደሉ፤ በህዝብ ስም እየማሉ ኢ-ህዝባዊ ተግባራትን እየፈፀሙ ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ እንጂ ህዝብን ለማገልገል ቆርጠው መነሳትን አያመላክትም።
በአጠቃላይ ወያኔ ኢህአዴግ ከስህተቱ የሚማር ቢሆን ኖሮ ባሣለፋቸው 27 ዓመታት ውስጥ ጉድለቶቹን አርሞ ወደ ተሻለ አገራዊ እና ዴሞክራሲያዊ መሪነት በተሸጋገር ነበር። ግን ስርዓቱ የሚፈልገው አንድና አንድ አላማ ብቻ ነው፣ ይህም ህዝብን በተለያዩ ስልቶች እያደናገረ፤ እያጣላና አንድነቱን እያፈራረሰ የስልጣን እድሜውን በማስቀጠል የአገሪቱንና የህዝብን ሃብት በመሟጠጥ ግላዊ ኪሱን መሙላት ካልሆነ የአገርና የህዝብ ጉዳይ ለአምባገነኑ ወያኔ ጉዳዩ አይደለም። ይህ ደግሞ አሁን የተፈጠረ ሣይሆን ከጅምሩ ይዞት የመጣው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለው አህያዊ አስተሳሰቡ ነው።
ስለዚህ ይህ የሲኦላዊ አስተዳድርን በአገራችን ላይ እየተገበረ ያለው የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ለህዝብ ጥቅምና ለሐገር አንድነት የቆመ ሳይሆን በህዝብ ስም እየማለ ኢ-ህዝባዊ ድርጊቶችን የሚፈፅም ስርዓት በመሆኑ በአስቸኳይ ከዚህ ተግባሩ መታቀብ አለበት ብቻም ሣይሆን በአስቸኳይ ከስልጣን ሊገረሰስ ይገባል።

No comments:

Post a Comment