Sunday, September 14, 2014

ለውጥ በትግል እንጅ በመልካም ፍላጎት ብቻ አይመጣም!



የኢትዮጵያ ህዝብ ለረጅም አመታት በላዩ ላይ ይደርስ ከነበረው ፌውዳላዊ ጭቆና ለመላቀቅ መጠነ ሰፊ ትግሎችን እያካሄደና በስርአቱ ላይ የነበረውን ከፍተኛ ጥላቻ በተለያየ መልክ ተቃውሞውን ይገልፅ እንደነበረ  ታሪክ  ሰንዶታል።
     የለውጥ መሪዎች የሆኑት ያገራችን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሃይለስላሴ ዘውዳዊ ስርአት በህዝቡ ላይ ሲያደርሰው የነበረውን ግፍና ጭቆና ከስሩ እንዲገረሰስ፤ ህዝቡ ከነበረው አስከፊ ያገዛዝ ቀንበር እንዲላቀቅና አጠቃላይ የፊውዳሉ አገዛዝ ተወግዶ ተራማጅ በሆነ ስርአት እንዲተካ ባጠቃላይ በተለያዩ ትምህርት ቤት የነበሩ ተማሪዎች በተለይ ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ለስርአቱ አገዛዝ እምቢ አሻፈረኝ ብለው በመቃወም የሂወት መስዋእትነት ከፍለው የስርአት ለውጥ በማምጣት ላይ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
     የወያኔ ኢህአዴግ ስርአት በኢትዮጵያ ህዝብ ትግልና መስዋእትነት ወደ ስልጣን ከወጣበት ግዜ ጀምሮም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች አሁንም ቢሆን  የሚያደርጉትን ትግል አላቛረጡም፣ በአዲስ አበባ፤ አምቦ፤ ሃረማያ፤ ጅማ፤ ባህርዳር መቀሌና በሌሎችም ቦታዎች የሚገኙ ተማሪዎች በወያኔ ስርአት እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰትና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አሰራርን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ተቃውሞዎችን በማቅረባቸው ብቻ በርካታ ንፁሃን ወገኖች እስርቤት ውስጥ ገብተው እየተሰቃዩ፤ እየተገደሉና ደብዛቸው እየጠፉ ይገኛሉ።
    ስልጣን ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ መንግስት 2007 ዓ/ም ላይ በተለየ መንገድ እየተዘጋጀበት ላለው አስመሳይ ምርጫ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ለሚጠረጠሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁል ግዜ ምርጫ በሚቀራረብበት ግዜ እንደሚያደርጉት አሁንም እንደወትሮው ከተማሪዎቹ ፍላጎት ውጭ በማስገደድ ለሳምንታት ያህል ሰፊ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ተጠምደው ሰንብቷል።
     የሚያስገርመው የስብሰባው አላማና ቀጥተኛ መልእክት ግልፅ እንደሆነ የሚታወቅ ነገር ቢሆንም እነዚህ ለስርአቱ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉት ወገኖች ከፍላጎት ውጭ በሆነ መንገድ እየተገደዱ ስብሰባ ላይ ቢቀመጡም በስርአቱ ካድሪዎች እየተሰጠ ያለውን የቅስቀሳ ትምህርት በመቃወም በህዝቡ ላይ እየደረሱ ያሉትን መጠነ ሰፊ ችግሮች በማንሳት ቁልፍ የሆኑ ጥያቄዎች ቢያቀርቡም የስርአቱ ካድሬዎች ግን በተማሪዎቹ እየቀረቡ የነበሩትን ጥያቄዎች የመመለስ ብቃትና ሞራል ስለሌላቸው ሁልግዜ እየተጠቀሙበት እንደመጡት ሁሉ ለጥያቄዎቹ በቂ መልስ ሳይሰጡ አድበስብሰው ማለፋቸው በተማሪዎቹ ዘንድ ቅሬታ አሳድሯል።
    በተማሪዎች እየተነሱ ከነበሩ ቁልፍ ጥያቄዎች ከፊሎቹን ለመጥቀስ።-
-    በሃይማኖት መሪዎች ላይ እየደረሱ ያሉ ፀረ ህዝብ ወንጀሎች ይቁሙ፤
-    ተቃዋሚ ድርጅቶችን ለመረጡ አርሶ አደሮች መሬታቸውን  እየነጠቅክ ለስርአቱ ካድሬዎች ማደል ተገቢነት የለውም፤
-    ሰፊውና ለም የሆነውን መሬታችንን ለውጭ ኢቨስተሮች አሳልፎ  መስጠት ያገራችንን ሉአላዊነት የሚጥስ ነው፣
-    ከአንድ ክልል ወደ ሌላው ክልል የሚደረግ የመሬት ሽግሽግ ህጋዊነት ያልተላበሰ አሰራር ነው፤
-    በኦሮምያ ክልል ውስጥ የምንሊክን ሃወልት ማሰራት ለምን ተፈለገ?
-    ኢህአዴግ እየገነበው ያለው መሰረተ ልማት እንስተኛ ነው፤
-    ገዢው የወያኔ ኢህአዴግ መንግስት በኪራይ ሰብሳቢነት እስተሳሰብ የተጨማለቀ ፀር ህዝብ ስርአት ነው የሚሉና ሌሎችም በርካታ ጥያቄዎች ማስነታቸው ይታወቃል፣
    የወያኔ ኢህአዴግ ካድሬዎች 2007 ዓ/ም ላይ የሚካሄደውን አስመሳይ ምርጫ ግምት ውስጥ ያስገባ በአቅም ግንባታ ስልጠና ስም በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ፤ መልካም አስተዳደርና አጠቃላይ አገሪቱ እየተመራችበት ያለችውን ፀረ ህዝብ ፖሊሲና ስትራተጂ አስመልክተው ሲያካሂዱት የሰነበቱትን ቅስቀሳ ቀኑ ያለፈበት ያረጀ ብልሃትና ሰዎችን ለማባበል እንዲሁም ለማደንገር የተካሄደ ሰብሰባ መሆኑን ራሳቸው ስብሰባው ላይ የተካፈሉት ተመሪዎች በሚገባ ገልፀውታል። 
     ለማጠቃለል ያገራችን ተማሪዎች ታሪክ ያገራችንን ስርአት የመለወጥ ታሪክ መሆኑን ይታወቃልና ያገራችን ወጣቶች ባጠቃላይ በተለይ ደግሞ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለውጥ በትግል እንጅ በበጎ ፍላጎት ብቻ እንደማይመጣ በመረዳት ልክ እንደበፊቱ ወንድሞቻችሁ ሲያነሱት የነበረውን የፀረ ጭቆና እንቅቃሴ በማስታወስና አላማቸውን በመከተል ለህዝብና ለሃገር  ፀር ለሆኑ የስርአቱ ሃይሎች በመቃወም አሁንም እንደትናንቱ የለውጥ መሪነታችሁን አጠናክራችሁ መቀጠል ይገባችኋል።