Tuesday, January 13, 2015

40ኛው የወሃት ልደት በዓልና የጥፋት ዝግጅቱ!!



    ህወሃት ኢህአዴግ 40ኛውን የልደት በዓሉን ለማክበር በማለት ካለፉት 39 ዓመታት ውስጥ ከነበረው በበለጠ ሽርጉድ በማለት ላይ ይገኛል።
 በዚህ መሰረትም ውጭ ከሚገኙት የዲያስፖራ ማህበረሰብ ኢትዮጵያውያን፤ አገር ውስጥ የሚገኙ የክልል መሰተዳድር ተወካዮችና ሲቪክ ማህበራት፤ በሁሉም ክልል የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች፤ አገራችን ውስጥ ከሚገኙት ታዋቂ አርቲስቶችና ፀሃፊዎች፤ ከትግራይ ውስጥም ቢሆን ከሁሉም ዞኖች፤ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የተወከሉ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በበዓሉ ላይ እንደሚገኙ ታውጇል፣ ለነዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶች ለማስተናገድ በሚሊዮኖች የሚገመት ወጪ እንደሚደረግ ለመገመት የሚያዳግት አይሆንም።
     በትራንስፖርት በኩል ባገራችን ውስጥ የሚገኙትን ምርጥ ኤም.ቢ.ኤም ኮብራ መኪናዎች፤አውቶብሶችና ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ተቛማት በዓሉ ላይ ለሚሳተፉ እንግዶች፤ የፌደራልና የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙበት ነዳጅ፤ ለእንግዶች የሚሰጥ የውሎ አበል ይክፍላሉ፤ ህዝብ በችግር አለንጋ እየተገረፈ ባለበት ግዜ እንግዶችን ተቀበል እየተባለ ከስራው እንዲሰናከልና ተገዶ መንገድ ላይ እየጨፈረ እንዲውል ማድረግ፤ ለማስመሰልና ህዝቡ በተመቻቸ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተደርጎ ለማቅረብ ለእንግዶች ተብሎ የተዘጋጀውን  ያገር ባህል ልብሶች፤ ሽርጦችና ሌሎችና ለሽልማቶች እየተባለ  የባከነው የሃገር ሃብትና ንብረት በገንዘብ ቢሰላ እጅግ በርካታ ገንዘብ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም።
   ህ.ወ.ሃ.ት ለልደት በአሉ ሲል እንዲህ አይነት ወጪ ሲያደርግ ዛሬ የመጀመርያው አይደለም፣ ወደ ስልጣን ከወጣበት እስካሁን ድረስ በቢልዮን የሚገመት የህዝብና የሃገር ሃብት አባክኗል፣ ይህ የሃገር ሃብት የማጠፋፋት ተግባርም በህወሃት ውስጥ ብቻ ታጥሮ የተወሰነ ሳይሆን። በሌሎች አጃቢ ድርጅቶችም የህወሃት ፈለግ በመከተል በብአዴን፤ ደኢህዴን፤ ዓፋር፤ ቤንሻንጉል፤ በሶማሌና ሀረሪ ድርጅቶችም ልደታቸውን ለማስከበር በሚል ምክንያት ከመጠን በላይ ገንዘብ ሲያባክኑ ይስተዋላሉ።
    ይህ በቢልዮን የሚገመት የገንዘብ ብክነት በሀገር ልማትና በድህነት ቅነሳ ስራ ላይ ቢውል ኑሮ የበኩሉን ድርሻ እንደሚኖረው የሚያጠያይቅ አይደለም፣ ነገር ግን የወያኔ ቡድን አመራሮች ይዘውት የተነሱት ዓላማ ህዝባዊ ሃላፊነት የሚያሸክም ስላልነበረ። የህዝቡን ጥቅም በሚያስከብር የልማት አስተሳሰብ ላይ እንዳይውሉ እንቅፋት እየሆነባቸው ይገኛል።
    ባሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ በድግሪና በዲፕሎማ የተመረቁ  ከ30 ሺ በላይ ስራ ያጡ ወጣቶች ይገኛሉ፣ 10፤ 12ኛና 8 ክፍል ላይ የወደቁ ተማሪዎች ስፍር ቁጥር የላቸውም ህወሃት ይህን ያህል ገንዘብ ለልደቱ ወጪ ከሚያደርግ በትምህርት ጥራት ማነስ ምክንያት የወደቁትን ተማሪዎች ማስተማርና ማብቃት በተገባው፣ ነገር ግን የህወሃት መሪዎች ከመጀመርያውም ማለት ትግል ከጀመሩበት ከየካቲት 11 ጀምሮ  ያነገቡት መፈክርና የትግል ዓላማ የህዝቡን ጥቅም የሚያስቀድም አልነበረምና በቢልዮን የሚገመት ይቅርና በትርሊዮን የሚገመት ብር ወጪ አድርገው በአሉን ቢያሳልፉት ደስታውን አይችሉትም።